የፓንዶራ ሳጥን

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

Pandoras-Box

በሚስጥረ አደራው

ሰው በተስፋ ይኖራል ይባላል፤የአለምን ውጣ ውረድ የህይወትን ፈተና ሰው ማለፍ የሚችለው ተስፋ መቀነን ሲችል ብቻ ነው፤ዕውቁ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን እንዲህ ሲል ሰው በተስፋ ይኖራል ይለናል።
“ተስፋ መቀነን ነው መቼም
የሰው ልጅ አይችለው የለም”
ጭንቀት እና ውጥረት በማይለያት በዚህች አለም፤እራስን ማዳን የሚቻለው ተስፋ ሲኖረን ብቻ ነው።ተስፋ መቁረጥ በቁም ከመሞት እንዳማይለይ እርግጥ ነው።ጥንታውያን ግሪኮች ስለተስፋ አንድ ድንቅ ታሪክ አላቸው…ታሪኩም እነሆ

“በድሮ ዘመን ጥንታውያን ግሪኮች የአማልክቶች ሁሉ ንጉስ ነው ብለው ያምኑበት የነበረው ዙስ የምድር ሰዎች እሳት እንዲኖራቸው አይፈልግም ነበር።ነገር ግን ሰዎችን እንዲሰራ ስልጣን ተሰጥቶት የነበረው ፕሮሚተስ እሳትን ከሰማይ ሰርቆ ለሰው ልጆች ሰጣቸው።ዙስ በዚህ አልተደሰተም እጅግም ተናደደ…ልቡም ለበቀል ተነሳሳ።ሰዎችን ለመቅጣት የተጠቀመበት ዘዴ ግን የሰዎችን ደካማ ጎን ነበር።ለበቀሉም ሲል የመጀመሪያዋን ሴት በምድር ፈጠረ..ይህች ሴት ፓንዶራ ትባል ነበር።የሰማይ አማልክት ሁሉ ካላቸው ነገር አንድ አንድ ስጦታ ሰጧት ….የስያሜዋ ትርጉምም “ሁሉንም ስጦታ የምትወስድ” ማለት ነው።ከሁሉም የተሰጣትን ስጦታ ግን ዙስ በሳጥን አድርጎ መቼም ቢሆን እንዳትከፍተው አስጠንቅቆ ነበር የሰጣት።ቁልፉን ቢያስረክባትም ሁሌም ይዛው ትዞራለች እንጂ እንዳትከፍተው ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ፓንዶራ ለሰዎች መቀጣጫ የተፈጠረች እንስት ነበረች።ዙስ ፓንዶራ ወደ ምድር ወርዳ እሳትን ሰርቆ ከዙስ ጋር ቅያሜ ከገባው ከፕሮሚተስ ወንድም ጋር እንድትጋባ አዘዘ።ፕሮሚተስ የዙስን ባህሪ ያውቃልና ለወንድሙ ከሰማይ አማልክቶች የሚመጣን ምንም አይነት ነገር እንዳይቀበል አስጠንቅቆት የነበረ ቢሆንም….ወንድሙ ግን የፓንዶራ ውበት አጓጓውና ተሸነፈ።
ፓንዶራ ከሰማይ ይዛው የመጣትችውን ሳጥን እንዳትከፍት የተሰጣት ማስጠንቀቂያ ከባድ ቢሆንም ጉጉቷን ግን ልትቆጣጠረው አልቻለችም።ምን ይሆን? እያለች ነፍሷን ሰላም አሳጣቻት።ባሏ የፕሮሚተስ ወንድም ማለት ነው….የአማልክቶቹን ትዛዝ እንድትቀበል እና ሳጥኑ እንደተቆለፈ እንዲቀመጥ ደጋግሞ ነገራት…ከእለታት አንድ ቀን ግን እሱ አብሯት ባልነበረበት ወቅት…ፓንዶራ ሳጥኑን ከፈተችው…ሳጥኑን ስትከፍ ግን ያገኘችው የአማልክቶቹን ስጦታ ሳይሆን …..የዙስን ቅጣት ነበር….ሳጥኑን የሞሉት አሁን አለምን የሚረብሿት እርኩስ መንፈሶች  ነበሩ….ፓንዶራ ሳጥኑን እንደከፈተችው….በሽታ …ክፋት…ምቀኝነት….ሃዘን….እየተነኑወጡ….ይህ ያስደነገጣት ፓንዶራ….ሳጥኑን እየተርበተበተች ለመዝጋት ሞከረች….ነገር ግን ሳጥኑን ስትዘጋ ዘግይታ ነበር….ሁሉም እርኩስ መንፈሶች ወጥተው ነበር….እናም ሳጥኑ ባዶ ሆኖ አንዲት መንፈስ ብቻ ቀርታ ነበር….ፓንዶራ ሳታውቀው ሁሉን ክፉ መንፈስ አስወጥታ….ያቺ አንዲት መንፈስ ላይ ብቻ ነበር የዘጋችባት….ያቺ መንፈስ ግን እርኩስ አልነበረችም…..ያቺ መንፈስ “ተስፋ” ነበረች።እናም ከዛን ጊዜ ጀምሮ… .መጥፎ ነገሮች ሁሉ የሰው ልጆች ጋር ደረሱ….ተስፋ ግን ሳጥን ውስጥ እንደተቆለፈባት ቀረች።

የፓንዶራ ሳጥን የእውነት ታሪክ ላይሆን ይችላል….ነገር ግን ከምንም በላይ አለም ላጣችው ተስፋ ጥሩ የመግለጫ ቋንቋ ይመስለኛል።ዙስ ሰዎች በጥርጣሬያቸው እንደሚጠፉ አውቆ ነበር። ተስፋ እና እምነት በአንድ አንገት ላይ እንደተሰሩ ሁለት ጭንቅላቶች ናቸው። ልክ ካህሊል ጆብራል ደስታ ሃዘንን እንደገለጸበት ማለት ነው።ተስፋ ባለበት እምነት አለ….እምነት ባለበት ተስፋ አለ።ደካማ አስተሳሰባችን ተስፋችንን እንደ ፓንዶራ ሳጥን ለብቻዋ ቆልፎባታል…ጥርጣሪያችንና ቀና ያልሆኑ አስተሳሰቦችን ሁሉ አስወጥቶ ተስፋን ብቻ ….ለብቻዋ ዘግቶባታል።

ተስፋን በልቡ ይዞ የሚጓዝ ሰው….መቼም ቢሆን ብቻውን እንደሆነ አይሰማውም….ብዙ እርቀትም ይጓዛል።ማን እንደተናገረው የማላስታው ሰው አንድ አባባል አለ “ ልብ ሲሞት ቀስ እያለ ነው….አንድ አንድ ቅጠሉን በየቀኑ እንደሚያጣ ዛፍ…በቀን በቀን ተስፋውን ሲያረግፍ ያኔ ልብ ቀስ እያለ ወደ ሞት ይጓዛል…ሁሉምቅጠሎችእረግፈውሲያልቁእናምንምተስፋሲቀርያኔ …የሰውልብምትሞታለች”

ተስፋ ከልባች አይጥፋ……..ተስፋ መቀነን ነው መቼም የሰው ልጅ አይችለው የለም ብሎ የለ ባለቅኔው!!! በተስፋ የማንችለው የለም። ተስፋችንን ለብዙ ጊዜያት እንደፓንዶራ በሳጥን  ቆልፈን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ኖረናል። እምነት፤ ፍቅርና መልካም አስተሳሰብ ተስፋችንን ከታሰረችበት ነጻ ሊያወጧት የሚችሉ ሃይሎች ናቸው።መጽሃፍ ቅዱስም እንዲህ ይላል “እምነት ተስፋና ፍቅር ጸንተው ይኖራሉ፤ ከሁሉም ግን ፍቅር ይበልጣል” ይላል። ምንም እንኳን ከሁሉም ፍቅር ቢበልጥም፤ ያለምክንያት ተስፋ ከእምነት እና ከፍቅር መካከል አልገባም። ተስፋ በእመነት እና በፍቅር መካካል የተዘረጋ ድልድይ ነውና።

Do you have any comments?