የሚታየውና የማይታየው ማዕበል

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

በሚስጥረ አደራው

stormsሰው ሃሳቡ በግንባሩ ላይ ቢጻፍ ማን ማንን ቀና ብሎ ያያል? ደግነቱ በውስጣችን ያለውን ማንም አያውቅብንም። የምናስበውን አስበን፤ የፈለግነውን አሳውቀን የምንደብቀውን ደብቀን የመኖር ጥበቡ ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ ጥበብ ነው። ልብ በሃዘን ደምቶ ፊት በፈገግታ ሲፈካ፤ ግንባር ኮስተር ብሎ ልብ በሃሴት ሲሞላ፤ ጉልበት ተንበርክኮ ልብ በትዕቢት ሲቆም፤ አፍ እንደ ማር ጣፍቶ ልብ እንደ እሬት ሲመር፤ ማን ማንን ያውቃል ያሰኛል።

ትላንት ጠዋት ወደ ስራ እየተጓዝኩኝ በስልኬ ላይ አንድ የውጭ አገር ሰባኪ (TD Jackes) እንዲህ ሲል ሰምቸው እጅግ ልቤን ነካው። “የሰው ልጅ በሚታየውና እና በማይታየው ማዕበል ውስጥ ያልፋል፤ የሚታየው ማዕበል ሌሎች የሚረዱት እና የሚያዩት ችግራችን ሲሆን፤ የማይታየው ማዕበል ደግሞ ከሌሎች ደብቀን ለብቻችን የምንጋፈጠው ችግር ነው”። ይህንን ስሰማ በህሊናዬ ውስጥ እኔን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተመላለሱ። ከተተኮሰው ልብሳቸው  ስር የተጨማደደው ልብ ያላቸው፤ ካማረው ቤታቸው ውስጥ የቆሸሸ ኑሮ ያላቸው ፤ ከበራው አይናቸው ስር የታወረ አስተሳሰብ ያላቸው ፤ ከቆመው ሰውነታቸው ስር ያጎነበሰ ማንነት ያላቸው ስንት ሰዎች አሉ? በአንጻሩ ካደፈው ልብሳቸው ስር የጸዳ ልብን የታደሉ፤ ከደሳሳው ጎጆዋቸው ውስጥ የደመቀ ኑሮ ያላቸው፤ ከታወረው አይናቸው ጀርባ የበራ አስተሳሰብን የታደሉ፤ ከጎበጠው ሰውነታቸው ውስጥ ቀጥ ብሎ የቆመ ማንነት ያላቸው ስንቶች ናቸው? እንደ ምጽዓት ቀን ስራችን እና አስተሳሰባችን በግንባራችን ቢጻፍ እንደማይተዋወቅ ሰው መተላለፋችን አይቀርም ነበር።

እኔ እንኳን ለመወቃቀስ አይደለም ይህንን ሃሳብ ያነሳሁት፤ አንዳችን የምንጋፈጠውን ማዕበል ሌሎቻችን ሳናውቅ ስለምንኖር ብዙ ስህተቶችን እንፈጽማለን።  በህይወቴ ተጽዕኖ አደረጉብኝ ከምላቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ በማይታይ ማዕበል ብቻውን የሚንገላታ ሰው መሆኑን ያወቅኩኝ ጊዜ፤ በማናውቀው የሰዎች ኑሮ ምን ያህል ስህተት የተሞላው ፍርድ እንደምንፈርድ ተረድቻለው። ይህ ሰው፤ ሰው ሁሉ የሚቀናበት (በመልካምም ሆነ በመጥፎ)  ነበር። ከላይ በግርድፉ ሲያዩት ሁሉ የተስተስተካከለለት፤ በስኬት ላይ ስኬት፤ በእውቀት ላይ እውቀት የተቸረው ምንም የጎደለው የማይመስል ሰው ነበር። የእጣ ፋንታ ጉዳይ ሆኖ ምንም እንኳን በእድሜያችንም ሆነ በምንም ነገር የሚያገናኘን ነገር ባይኖርም፤ ተገናኘንና ማንም የማያውቅለትን የውስጡን ቁስል በአንደበቱ ተረከልኝ። ለዚህ ነው ትላንትና ወደ ስራዬ ሳቀና የሰማሁት የሰባኪው ንግግር ልቤን የነካው።

ሌሎች የማውቁት ምን አይነት ጭንቀት ይሆን እያንዳንዳችን በውስጣችን ያለው? ምን አይነት የማይታይ ማዕበል እየተጋፈጥን ይሆን? ልክ እንደ ዘሪቱ ዘፈን

“ቀን ቀን ስራ አይጠፋም አስሮ የሚያስውለኝ፤

የማያስተክዘኝ የማያሳስበኝ

ሲመሽ ግን ችግር ነው ሰማዩ ሲጠቁር….” እያልን ኑሮዋችንን የምንገፋው ሁላችንም ነን። ይህች አጭር ጽሁፍም የማይታየውን ማዕበል ለብቻቸው ለሚገፈጡ ምስኪኖች እንዲሆንልኝ እጠይቃለው፤ ሰው የሚያየውን ማዕብል የሚገፋጡት አጋዥ አያጡምና።

 

አዎ በሰው ፊት እንስቃለን ለብቻችን ግን እንባችንን በገዛ መዳፋችን ያለማቋረጥ እናብሳለን። ከሰው መሃል ደምቀን ለባቻችን ስንሆን መግቢያ እናጣለን። ከህዝብ ፊት ከብረን በቤታችን ግን የሰው ያህል የሚቆጥረን የለም። ጠንካራ መስለን፤ ልባችንን ግን በክህደት ስብርብሩ ወጥቷል። ከላይ ሰላም የሰፈነብን እንመስላለን፤ ውስጣችን ግን በተስፋ መቁረጥ ማዕበል ይተራመሳል። ከውጪ ሲታይ ቤታችን የደመቀ ቢመስልም ውስጡ ግን እንደ ዋሻ ቀዝቅዟል። እንዲህ የምንኖረው እኔ ወይም ጥቂቶቻችን ብቻ ሳንሆን ሁላችንም ነን ብዬ አምናለው። ተለቀም አነሰም ሁላችንም ለሌሎች የማይታይ ለብቻችን የምንጋፈጠው ማዕበል አለን። እናም በየመንገዳችን ስንተላለፍ ልብ እንበል፤ ሌላው ከኛ ያነሰ ትግል የሚታገል እየመሰለን ፊት አንንሳው፤ እየረገጥን አንለፈው።

 

የኔ ችግር እና ጭንቀት ከሌላው ይበልጣል የሚል አስተሳሰብ ሲኖረን ለሌሎች የምንዘረጋው እጅ ያጥረናል። ትኩረታችን ሁሉ የራሳችን ችግር ላይ ሲሆን ይበልጥ እናማርራለን፤ ሌሎች ለብቻቸው የሚገፈጡትን ማዕብል ስለማናይ “ምነው እኔን ብቻ” እያለን የሃዘናችንን ጉድጓድ ይበልጥ ወደታች እንቆፍረዋለን። ከትዳር አጋራችን ጋር ክንድ ተንተርሰን እያደርን፤ እርስ በርሳችን የምንፋለመውን ትግል አናውቅም። ለዚህ ነው ጭቅጭቅ ሲነሳ መሸናነፍ እና እርቅ ማውረድ የሚከብደን፤ ማን የማንን ማዕበል ያያልና?

እናም በየመንገዳችን የሚያጋጥሙን ሰዎች ሁሉ የራሳቸው የሆነ ታሪክ አላቸው፤ በጫማቸው ሳንቆም አንፍረድ። በደቂቃ ውስጥ ያየነውን ምግባራቸውን ተንተርሰን አንፍረድ። ሌላውም እንደኔ ስሜት አለው የሚል አስተሳስብ መያዝ ስንጀምር፤ የሌላው ህመም ይሰማናል እናም ብዙ ስህተቶችን ከመፈጸም እንድናለን። ምናልባት ለብቻሽ/ለብቻህ የምትጋፈጠው ማዕበል ካለህ በርታ……..አጋዥ የለኝም ብለህ አትስጋ ፈጣሪ የማትችለውን ችግር አይሰጥህም። አንተ/አንቺ ብቻ ከሰው የተለየ መከራ አልተሰጠሽም/አልተሰጠህም እንደየአቅማችን ለሁላችንም የታደለን ነው እንጂ……ከምንም በላይ ግን እርስ በርሳችን እንተጋገዝ፤ እየተገፈታተርን መተላለፉን እናቆም ምክንያቱም ሁላችንም  ለየብቻችን በምንጋፈጠው ማዕበል ደክመናልና።

Do you have any comments?