ሌሎች ስላንተ ያላቸው አስተያየት ማንነትህ እንዳይመስልህ ተጠንቀቅ

Posted on Posted in መነቃቂያ

በአሁኑ ሰዓት ስለራሳችን ያለን አስተሳሰብ ከየት እንደመነጨ ጠይቀን እናውቃለን? ስለራሳችሁ ተናገሩ ብንባልስ ምን መልስ ይኖረናል? አቅማችንንስ ስንመዝን በማን መመዘኛ ነው? እንችላለን ብለን የምናስባቸው ነገሮችም ሆኑ አንችላቸውም ብለን የምናስባቸው ነገሮች በመጀመሪያ እንዴት ወደ አይምሮዋችን ዘለቁ?

ይህንን ያልኩበት ምክንያት ብዙዎቻችን ያለንን አቅምም ሆነ ተሰጥዎ አውጥተን ያልተጠቀምንበት ዋነኛው ምክንያት ሌሎች በአንድ ወቅት እንደማይቻል ሹክ ስላሉን ነው ወይም ብቁ እንዳልሆንን ስላሳመኑን። በተለይ የሚወዱን እና የምንወዳቸው ሰዎች፤ እምነት የጣልንባቸው ወዳጆች ሳያውቁ በህሊናችን ውስጥ እውነተኛውን ማንነታችንን የሚያደበዝዝ አሻራ ሊያኖሩብን ይችላሉ።

ስንቶች ናቸው በልጅነት ጓደኞቻቸው ተስቆባቸው ነፍስ አውቀው እንኳን ማንነታቸውን ለመቀበል የሚከብዳቸው? አንድ የትምህርት አይነትን ስለወደቁ ብቻ በመምህራቸው “ደደብ” ተብለው እድሜ ልካቸውን ደደብ እንደሆኑ አምነው ሳይበሩ የከሰሙ ስንት ሰዎች አሉ? በተለይ በልጅነታችን እንደዘበት የሚወረሩብን ቃላቶች ምን ያህል የወደፊቱ ህይወታችንን እንደሚቀርጹት  የማያስተውሉ ብዙዎች ናቸው።

ሁሌም ይህንን አስተሳሰብ በደንብ የሚገልጽልኝ ታሪክ አለ። በአንድ ወቅት አንድ ጎብኚ ትልቅ የእንስሳ ማዕክለን ሲጎበኝ እጅግ የሚገርም ነገር ያስተውላል። አንድ ትልቅ ዝሆን በቀጭን ገመድ ታስሮ ይጎበኛል (ለማምለጥ ሳይሞክር)። ገመዱ እንኳን ያንን የሚያክል ዝሆን ይቅርና ዶሮንም በቅጡ የሚያስር ጠንካራ ገመድ አይደለም። ይሄኔ በማዕከሉ የሚሰራውን አንድ ሰው ተጠግቶ እንዲህ ሲል ጠየቀው “ቆይ ይህንን የሚያክል ዝሆን እንዴት በዚህች በምታህል ገመድ ብቻ ታስሮ ይቆያል? ገመዱን በማንኛውም ሰዓት በጥሶ ማምለጥ ሲችል” አለው። ሰራተኛውም እንዲህ ሲል መለሰለት “ይህ ዝሆን አሁን የታሰረበት ገመድ ትንሽ እያለ የታሰረበት ገመድ ነው፤ ትንሽ እያለ ገመዱን በጥሶ ማምለጥ አይቻለውም ነበር። ያንን አይምሮው አንዴ ስላመነ ምንም ያህል ቢገዝፍም ለማምለጥ አይሞክርም” ብሎ አስረዳው።

ምንም ያህሎቻችን ነን በልጅነት ገመዳችን እስካሁን የታሰርነው? ሌሎች ሳያውቁ ባጠለቁብን ገመድ መሄድ ከሚገባን የተገታን ጥቂቶች አይደለንም። እንደዘበት የተሰነዘረብን አስተያየት እውነተኛ ማንነታችን መስሎን የማንደሰበትን ኑሮ እንኖራለን። “አትችልም” ስለተባልን አንችልም ብለን አምነናል። “አስቀያሚ” ስለተባልን ውበታችንን ማየት ተስኖናል። “ደደብ” ስለተባልን ለም አይምሮዋችንን ሳንጠቀምበት ቀርተናል። ልዩ በመሆናችን ጥቂቶች ስለተሳለቁብን ብቻ ከሰው የማንገጥም እየመሰለን እራሳችንን አግልለናል።

አስታውሳለው ከአመታት በፊት አንድ ጓደኛዬ መቼም የትዳር ጓደኛ የሚኖረኝ እንደማይመስላት ስትነግረኝ እርግጠኝነቷ ፊቷ ላይ ይነበብ ነበር። ለብዙ ጊዜያትም እውነት መስሎኝ ኖሬያለው። አይምሮዬ ነገሮችን ማስተዋል ሲጀምር ግን ሌሎች ስለኔ ያላቸው አስተያየት የኔ ማንነት እንዳልሆነ ተረድቻለው።ሰዎች ስለኛ አስተያየት ሲሰጡን ከምን ተነስተው እንደሆነ አናውቅም። እኔ በክፋት አልወስደውም  አልያም በምቀኝነት፤ ነገር ግን ካለማወቅ ነው ብዩ አምናለው። እንደቀልድ ብዙ ሰዎች በህይወታችን ውስጥ ገመድ አጥልቀውብናል። ያኔ አይምሮዋችን ስላልበሰለ ማምለጥ አቅቶን ይሆን ይሆናል። እናም አሁንም ድረስ እራሳችንን ነጻ ማውጣት የማይቻል እየመሰለን እንደ ዝሆኑ በቀጭን ገመድ ታስረናል።

አንተን ወይም አንቺን ያሰረሽ ምንድን ነው? ሌሎች የሰጡህ ወይም የሰጡሽ አስተያየ እውነት ነው ብለሽ/ብለህ እየኖርክ ነው? ማንነታችን እኛ እንመርጠዋለን እንጂ ሌሎች ሊመርጡልን አይችሉም። ሳያውቁ በመንገዳችን የቆሙትን ሰዎች ይቅር ብለን፤ የምንፈልገውን ኑሮ እንዳንኖር ያሰረንን ያንን ቀጭን ገመድ እንበጥስ። በዚህ ምድር ላይ ከፈጣሪ በታችን ካንተ በቀር ያንተን ህይወት በሃላፊነት ሊወስድ የሚችል ማንም ሰው የለምና።

በመጨረሻ ለሰዎች የምንነግራቸውን ነገር እናስተዋል፤ እንደዘበት የሚያስራቸው ገመድ ሊሆን ይችላልና!

Do you have any comments?