መዳፎቹን በትናንት ህይወቱ የሞላ ሰው፤ ነገን እንዲት ሊቀበል ይችላል?

Posted on Posted in መነቃቂያ

“when you hold on to your history, you are doing it at the expense of your destiny” T.D Jakes

እርግጥ ነው የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ልክ ዘፋኙ እንዳለው። ዛሬያችን ትናንት ላይ በወሰንናቸው ውሳኔዎች የተገነባ ነው። ስለትናንት ማሰብ ባልከፋ ምክንያቱም ከስህተታችን ትምህርትን ከስኬታችን ብርታትን እስካገኘንበት ድረስ። ባሳለፍነው ህይወት ውስጥ የምንደሰትበት እንዳለ ሁሉ የሚጸጽቱንም ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ስህተትን የማይሰራ ሰው ኑሮን እየኖረ ነው ለማለት ይከብዳል። በየትኛውም የህይወት አቅጣጫ ብንጓዝ ስህተት ለመፈጸም ዝግጁ መሆን አለብን። የሰው ልጅ ጥንካሬው በወደቀ ቁጥር መነሳቱ፤ ስህተት በሰራ ቁጥር ብርታት ማግኘቱ ነው።

ዛሬ እንደንወያይበት የመረጥኩት ርዕስ ግን እራስን በጸጸት ስለመጉዳት ነው። አለመታደል ሆነ ምንም ያህል የይቅርታ ሰዎች ብንሆንም ለሌሎች ይቅርታ እያደረግን ለገዛ እራሳችን ግን ይቅርታ ማድረግ ይከብደናል። እራሳችን ላይ እንጨክናለን። ትላንት የወደቅንበት ጉድጓድ ዛሬ ጥልቀቱ አንገታችን ላይ ቢደርስም እንኳን ለመውጣት ይከብደናል። ነጋችን ከትናንታችን ጋር ቁርኝት ያለው እየመሰለን ተስፋችንን በአጭሩ እንቀጫታለን።

ከላይ የሰፈረውን አባባል ለኛ እንደሚመቸን አድርገን ብንተረጉመው፤ የትናንት ህይወቱን በመዳፉ ጨብጦ  የሚኖር ሰው አዲስ ኑሮና ህይወት ለመቀበል ቦታ አይኖረውም እንደማለት ነው። ለምሳሌ በሁለቱም መዳፎቻችን ድንጋይ ይዘን፤ ዳቦ የሚሰጠን ሰው ብናገኝ እንዴት ልንቀበለው እንችላለን? በህይወታችንም ውስጥ ተመሳሳይ ነገር የምናድርግባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው።

ለምሳሌ ትናንት በበደሉን ሰዎች ቂም መዳፋችን ይሞላና፤ ሌሎች ፍቅር ሲቸሩን መቀበል ያቅተናል። ትናንት ያልሰመረውን ጓደኝነት ትዝታውን በጎዳናችን ይዘን ስለምንጉዝ  አዲስ ጓደኛ በመንገዳችን እንዳናፈራ እንቅፋት ይሆንብናል ። ትናንት ያልሰመረው ትዳር ዛሬም ትዝታው ከቤታችን ስላልወጣ አዲስ ፍቅር ወደ ቤታችን እንዳይገባ አግዶታል። ምክንያቱም መዳፎቻችን በትናንት ትዝታ ስለተሞሉ አዳዲስ ስጦታዎችን መቀበል አልታደልንም።

በስራ ህይወታችንም እንደዛው የትናንት ውድቀታችንን ይዘን ስለምንዞር አዲስ ነገር ለመሞከር ብርታቱን እናጣለን። መዳፋንች ሁሌም በትዝታ እና በጸጸት ስለሚሞላ ዛሬ እና ነገ የሚያቀርቡልንን ስጦታዎች ለመቀበል ቦታ የለንም። ይህንን እየጻፍኩኝ የማዲንጎ የተዝታ ዘፈን ትዝ አለኝ

አግኝቶ ላያገኝ ወይ ጠቅሞ ላይጠቀምው

 ሰው ለምን ይኖራል ትዝታ  ሲያደክመው

ይኸው ሰው ይኖራል በትዝታ ሰበብ

የኋሊት ሲጋልብ ትናንት በማሰብ

ሰው እንዴት ባለፈው በትናንት ይኖራል

ዛሬን በእጁ ይዞ ለነገው መሰላል

ትዝታ ልሳብሽ ታይኝ

አትጋርጂኝ ልይበት የነገን ተስፋዬን

ባይጠፋም አሻራው ትዝታው ቢነስፍም

ባለፈ አመት ዝናብ ዛሬ አይታረስም………”

ታዲያ  እዚህ ላይ ትዝታ ሁሉ መጥፎ ነው እያልን አይደለም። ደግመን ደጋግመን በህሊናችን የምንስላቸው ብዙ መልካም ትዝታዎች አሉ። ነገር ግን ትዝታችን ጉልበት አግኝቶ የኋሊት  እስኪያስጋልበን ድረስ ግን መታገስ የለብንም። እውነት የሰራናቸው ስራዎችን እና ጥፋቶችን ልክ ምጽዓት ቀን በግንባራችን ላይ ቢጻፉ፤ እርስ በርሳችን ቀና ብለን ለመተያተ ባልቻልን ነበር። አንዳንዶቻችን ከተዘፈቅንበት አዘቅት መውጣት ያልቻልነው ስህተታችንን አግዝፈን በማየት አዲስ ኑሮ መኖር የማይቻል ስለሚመስለን ነው።

ምናልባት የትናንት ህይወትህ መጥፎ ሊሆን ይችላል። ለራስህ ይቅርታ ማድረግ ከቻልክ ግን፤ አዲስ ህይወት ለመጀመር ምቼም ቢሆን አትዘገይም። ይልቅ በጸጸት ጊዜህ አታባክን፤ ባለፈ አመት ዝናብ ከቶ አይታረስምና።

Do you have any comments?