ፍቅር እና ነጻነት

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

“Love one another, but make not a bond of love: Let it rather be a moving sea between the shores of your souls.” ―ካህሊል ጂብራን

እያንዳንዳችን ፍቅርን የምንገልጽበት የራሳችን የሆነ መንገድ አለን። እናትና አባት ለልጆቻቸው፤ ወንድም ለእህቱ፤ እህት ለወንድሟ፤ ጓደኛ ለጓደኛ፤ ሚስት ለባሏ፤ ባል ለሚስቱ፤ ፍቅራቸውን በተለያየ መጠንና መንገድ ይገልጹታል። ዛሬ በትንሹ ልጽፍበት የፈለግኩት ርዕስ የፍቅርን መጠንና አይነት ሳይሆን፤ ፍቅራችንን ስለምንገልጽበት መንገድ ነው። በፍቅር ስም ብዙ ስህተቶች ሲፈጸሙ ይስተዋላል። ፍቅር ስህተት ሆኖ ሳይሆን የሚገለጽበት መንገድ ልክ ስላልሆነ ብቻ። ምክንያቱም ፍቅር ምን ጊዜም በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ስህተት ሆኖ አያውቅም።

ፍቅር ጉዳት የሚሆነው፤ ስህተት የሚመስለው የሰዎችን ልብ የሚሰብረው፤ ፍቅር ስህተት ሆኖ ሳይሆን ያስተላላፊው ስህተት ሲኖር ነው። ፍቅርን ልክ እንደ ንጹህ የሃይቅ ውሃ ውሰዱት፤ እያንዳንዳችን የራሳችን የሆነ ማስተላለፊያ መንገድ መንገድ አለን። ያንዳንዶቻችን ቱቦ ንጹህ ፤ ያንዳንዶቻችን ቆሻሻ ፤ ያንዳንዶቻችን ጠባብ፤ ያንዳንዶቻችን ሰፊ ይሆንና ፍቅር መልኩን እየቀያየረ የሚመጣ ያስመስሉታል።

ፍቅር ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ለመተላለፍ ነጻነትን ይፈልጋል። ነጻነትን የተነፈገ ፍቅር ለተቀባዩ እዳ ይሆናል። አንዳንዴ የምንሰማው ነገር ግራ ያጋባል፤ ለምሳሌ አንድ ወንድ አንዲት ሴትን ወዶ ምላሿን ከነፈገችው እስከ ግድያ ይደርሳል። ይህ እውነተኛ ፍቅር ነው ሊባል ፈጽሞ አይችልም። ፍቅር በአስተላላፊዎቹ ስሀትት ንጽህናው ይበረዛል። ለሚስቶቻቸው ያላቸውን ፍቅር በቅናት የሚገልጹ ባሎች ጥቂት አይደሉም። ለባሎቻቸው ያላቸውን ፍቅር በመጨቃጨቅ የሚገልጹ ሚሶችም እንደዛው።

ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ አለቅጥ ሲቆጣጠሩ በልጅ እና በወላጅ መካከል ያለው የግልጽነት ድልድይ ይሰበራል። ወላጅ ፍቅሩን “እኔ አውቅልሃለው” በሚል አገላለጽ ሲገልጽ ልጆች በወላጅ ተጽዕኖ ነጻነታቸውን መስዋት ያደርጋሉ። ይህ ማለት ወላጆች ልጆቻቸውን መቆጣጠር የለባቸውም ሳይሆን፤ እስከምን ደረስ መሆነ እንዳለበት ልብ ሊባል ይገባል። ወላጅን ፍራቻ ልጆች ብዙ ስህተቶችን ይፈጽማሉ። ውድቀታቸውን እና የህይወት ፈተናዎቻቸውን  ለወላጆቻው መግለጽ የሚከብዳቸው፤ ወላጆች ፍቅራቸውን የገለጹበት መንገድ ልክ ባለመሆኑ ነው። በተለይ በኛ ማህበረሰብ ግልጽነት የሚጎድለን፤ ወላጆቻችን ፍቅር አንሷቸው ሳይሆን አገላለጻቸው ወደ ፍርሃት ስለሚወስደን ነው። ካህሊል ጂብራን ወላጆች ለልጆቻቸው ነጻነትን ለምን መስጠት እንዳለባቸው እንዲህ ያስረዳል “Your children are not your children. They are the sons and daughters of Life’s longing for itself” ― ካህሊል ጂብራን.

በየትኛውም ቦታ እና ግንኙነት ፍቅር ህይወት ሊዘራ የሚችለው ነጻነት ስኖረው ብቻ ነው። ኦሾ እንዳለው የምንወደውን ጽጌሬዳ ቆርጠን አናስቀምጠው ምክንያቱም ይሞታልና። ይልቁንም እውነተኛ ፍቅር ካለን ባለበት እንዲያብብ እንፈቅድለታለን። የምወዳቸውን ሰዎችም ማስተናገድ ያለብን እንዲህ ነው፤ እውነት የምንወዳቸው ከሆነ ነጻነታቸውን እንስጣቸው። በፍቅር ስም እነሱ የመረጡትን ሳይሆን እኛ የመረጥልናቸውን እንዲኖሩ አናስገድዳቸው። በዚህም ምድር ላይ ለሰው ከነጻነት የበለጠ ስጦታ የለም። በነጻነት ውስጥ እምነት አለ በራሷ እንደትበር የተለቀቀች ወፍ ሌሎች በሷ እንደሚያምኑ ይሰማታል። በነጻነት ውስጥ ግልጽነት አለ፤ የሚሸፈን የሚከደን ምንም ነገር ስለሌለ። ፍቅር ደግሞ ያለእመነት እና ግልጽነት ዋጋ አይኖረውም።

ለዚህ ነው ፍቅር እና ነጻነት ተለያይተው መሄድ የማይችሉት። የምንወዳቸውን ሰዎች እናስብ ፍቅራችንን እንዴት እየገለጽንላቸው ነው? ነጻነታቸውን በሚጋፋ መልኩ ከሆነ እስቲ ትንሽ እናስብበት።

Do you have any comments?