በስተመጨረሻ ይዘነው የምንሄደው ምንድን ነው? ‪

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

“At the end it’s not the years in your life that count, it’s the years in your life” -Abraham Lincoln

ጠቢቡ ሰለሞን ሁሉን አየ ሁሉን አጣጣመ በስተመጨረሻ “ሁሉም ከንቱ ነው የከንቱ ከንቱ፤ ነፋስንም እንደመከተል ነው” ሲል ኑሮን ደመደመ። እንደኔ ሁሉም ከንቱ ነው ሲል ተስፋ ሊያስቆርጠን አይመስለኝም፤ ተስፋን ሊሰጠን እንጂ። ህይወታችን ከማንኛውም አለማዊ ሃብት፤ ከማንኛውም ዝና ከማንኛውም ክብር የላቀች መሆኗን ሲነግረን ይመስለኛል። ይህንን በቅጡ መረዳት ስለሚሳነን፤ በስተመጨረሻ ይዘናቸው በማንሄዳቸው አላፊ ነገሮችን ኑሮዋችንን እንበጠብጣለን።

ኑሮ ማለት በውልደት እና በሞት መካከል ያለ የመሸጋገሪያ ጊዜ ነው። በድንገት ተጀምሮ በድንገት የሚቆም የመሸጋገሪያ ጊዜ። ጥቂቶች ይህንን የተረዱ ጊዜያቸውን አጣጥመው ይኖራሉ። አብዛኛዎቻችን ግን ዘላለም እንደሚኖር ሰው ተዘናግተን እንኖራለን። ሳንስቅ ሳንጫወት ፤ መልካም ነገር ሳናደርግባቸው በተራ ነገር የሚያልፉ ቀናቶች ከቆምንበት ህንጻ ስር እየተሸረፉ እንደሚወድቁ ጡቦች ይቆጠራሉ። ቀስ እያሉ ከከፍታው የሚያወርዱን።

ሁሉም ከንቱ ነው የከንቱ ከንቱ ምክንያቱም ምንም ነገር በሞት ፊት ቆሞ ሞትን የሞጋፈጥ ነገር ስለሌለ። ይህን የተረዳ ሰው ትልቁን ቀንበር ከላዩ ላይ አወረደ ማለት ነው። የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ከልቡ ያደርጋል ምክንያቱም እድሉ አንደ ብቻ እንደሆነች ስለሚረዳ። እውነት ከሞት ፊት ቆሞ በቀልን የሚያስብ ማነው? ከመቃብሩ ላይ ቆሞ ገንዘቡ የሚያሳሳው ማነው? በከፈን ውስጥ ሆኖ የሚጠላውን ሰው የሚያስብ የሚቀና ማን ነው? በእርግጠኝነት ማንም። በሞት ፊት ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፤ የከንቱ ከንቱ።

በስተመጨረሻ ይዘነው የምንሄድ ምንም ነገር የለም።ይልቅ የመሸጋገሪያ ጊዜያችንን መልካም እናድርገው። ተሰጥዖችንን እናበርክት፤ ማናችንም ያለተሰጥዖ አልተፈጠርንም። ተራ ሆነን መሞትን አንምረጥ። የራሳችንን አሻራ አኑረን፤ ነበሩ ለመባል ያብቃን። ሰለሞን ከንቱ ናቸው ያላቸው ነገሮች ህይወታችንን የሚያጨልሙና የምድር ቆይታችንን መራራ የሚያደርጉትን ነገሮች ነው። ህይወታችን ክቡር ናት፤ ከማንኛውም ነገሮች ሁሉ የከበረች የፈጣሪ ስጦታ። እኛ ግን በኪሳራ እየቸረቸርናት ነው። ፍቅር የሌላት ህይወት፤ እምነት የራቃት ህይወት፤ ሰላም የጎደላት ህይወት፤ ደስታ የሌለባት ህይወት ያለዋጋዋ የተሸጠች ናት። ምክንያቱም በዚህ ምድር የህይወታችንን ዋጋ የሚስተካከል አለማዊ ነገር ስለሌለ።

 

 

One thought on “በስተመጨረሻ ይዘነው የምንሄደው ምንድን ነው? ‪

Do you have any comments?