ጭካኔ፤ ስልጣኔ ወይስ እምነት?

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

ሞትን የማይፈራ ማነው? ምንም እንኳን አለም ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ የኖረ ነገር ቢሆንም፤ በፍጹም የሚለመድ አይደለም። ሁሌም እንግዳ ነው፤ ሁሌም ሃዘኑ ትኩስ ነው። ስቲቭ ጆብስ ለአመታት ጠዋት ጠዋት ቀኑን ከመጀመሩ በፊት ለራሱ የሚናገረው አንድ አባባል እንደነበረ  በየሚዲያዎቹ ተናግሯል አባባሉም ይህች ነበረች “ዛሬ የህይወትህ የመጨረሻ ቀን ቢሆን ምን ታደርግ ነበር?” እያለ እራሱን እንዳያንቀላፋ፤ የደመነፍስ ኑሮ እንዳይኖር ዘወትር ያነቃው ነበር።

ስለሞት እንዳስብ ያደረገኝን አጋጣሚ ላጫውታችሁ። ሁለት ሴቶች  አምረው እና ደምቀው ወደመደብሩ ይገባሉ፤ ፈገግታቸው ሳይጨፈግግ ለሴቶች የሚሆን ማጌጫ ለመሸመት አይናቸውን ያንከራትታሉ። አጠገባቸው ነበርኩኛና፤ በስልካቸው ላይ ያለውን የታዋቂ ፊልም ተዋናይ ያደረገችውን ጌጥ እንደሚፈልጉ ጠየቁኝ። የገመትኩት እንደባህላቸው ወይ ለፓርቲ አልያም ለሆነ ፕሮግራም ፈለገውት ይሆናል ብዬ ነበር። ነገር ግን ከአነጋገራቸው ለሌላ ሶስተኛ ሰው እንደሚገዙ ገባኛና ለማን እንደሆነ ጠየቅኳቸው። እነሱም “አይ እናታችን ሞታ ለብሳው የምትቀበረውን ልብስና ጌጣ ጌጥ እየሸመትን ነው፤ ኸረ እንደውም የገዛነውን ልብስ አናሳይሽ” ብለው፤ እሬሳ ሳጥን ላይ የተደገፈ ውብ ነጭ ልብስና የአንገት ጌጥ አሳዩኝ። አስተያዬት ፈልገው……..

ደንገጥኩኝ የኛን ሃገር ለቅሶ እና ሃዘን አስቤ ግራገባኝ። እኛ ሃገር እናቱ ሞታ ጌጣጌጥ ሽመታ የሚሄደው ማን ነው? ምዕራብያኑ ሞትን እንዲህ በተረጋጋ መንፈስ እንዲቀበሉት የሚያደርጋቸው ነገር ስልጣኔ ነው? ጭካኔ ነው? ወይስ እምነት። የራሴን ጥያቄ እራሴ ስመልስ ሶስቱም መልስ ሊሆን እንደሚችል ቢገባኝም ወደ እምነት ማድላቱን መረጥኩኝ።

ትክክል እና ስህተት የስምምነት ጉዳዮች ናቸውና ይህ ትክክል ነው ይህ ደግሞ ስህተት ነው ለማለት አልደፍርም። ነገር ግን የሰው ልጅ ትልቁ መነቃቂያው ሞቱ ነው ብዬ አምናለው። ኑሮዋችን የኮንትራት ነው፤ አለመታደል ሆኖ ኮንታራትችን መቼ እንደሚያልቅ አናውቅም። የተቻለንን ያህል መኖር ከቻልን ግን የሞት ግዘፈቱ ሳይቀንስ አይቀርም። እየሳቁ የሞቱ ብዙዎች ናቸው፤ ድል የተመቱ ሳይመስላቸው፤ በኮንትራታቸው ላይ የተዋዋሉትን በአግባቡ እደፈጸሙ ተሰምቷቸው የሚሞቱ ጥቂቶች አይደሉም።

ዋናው ነቅቶ መኖር ነው፤ መጽሃፍ ቅዱስ እንዲህ በቃሉ ያነቃናል “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንደሚመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ፤ ያን ግን እወቁ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃ ቤቱንም ባልተወም ነበር፤ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” ይላል።

ብዙ ነገሮችን በቀጠሮ የመያዝ ልምዱ አለን። ከሰው ጋር ተቀያይመን ይቅርታችንን በቀጠሮ ይዘን ሰላም ሳናሰፍን ሌባው ይቀድመናል። ደስታችን  በነገሮች ላይ ተንጠልጥሎ፤ ይህ ሲሳካ እደሰታለው በማለት ለመደሰት ቀጠሮ እንደያዝን ሌባው ቀድሞን ይደርሳል። ህይወት ምንም አይነት ዋስትና የላትም፤ ዛሬን መኖር ያልቻለ ሰው ሁሌም ከነገ ጋር ቁማር እየተጫወተ ነው፤ ወይ ይበላል (በ ሲጠብቅ) አልያም ይበላል። በብዛት ግን ይበላል (በ ሲጠብቅ)። ስለሞት በማሰብ ሃዘን እንዲሰማን አያስፈልግም፤ ይልቁንም ነቅተን ያቅማችንን እንድንኖር ይረዳናል እንጂ። እንሞታለን ማለት አላማ ሊኖረን አይገባም ማለት አይደለም፤ እንደውም ስለምንሞት አላማ ሊኖረን ይገባል……..

Do you have any comments?