እራሳችንን ይቅር እንበለው!!! ይቅርታን ከጠየቀ……..

Posted on Posted in መነቃቂያ

ወቀሳ ለማንም ጠንካራ ነኝ ለሚል ሰውም ከባድ ሸክም ነው። ሌሎች ሲወቅሱን፤ ከጥፋታችን በላይ ሊቀጡን ሲሞክሩ ምን ይሰማናል? ወቀሳ እረፍት የሚነሳ፤ የሚያሸማቅቅ፤ ዝቅተኝነት እንዲሰማን የሚያደርግ ስሜት ነው። የሚገርመው ብዙን ጊዜ ከሌሎች ሰዎች ዘንድ የሚመጣውን ወቀሳ ነው እንጂ፤ እኛ በገዛ እራሳችን ላይ የምናዘንበውን ወቀሳ  አስተውለነው አናውቅም። ሃዘናችን በብዛት የሚመነጨው እራሳችንን ይቅር ካለማለት ነው። ለስህተታችን ይቅርታን ስንፈልግ፤ ሌሎች እንዲምሩን እንጂ ከራሳችን መምጣት ስለሚገባው  ምህረት አናስብበትም። ኸረ እንደውም አንዳንዶቻችን እራሳችንን ይቅር ስለማለት ምንም አይነት ግንዛቤው የለንም።

ያለናንተ መኖር የማይችል ብቸኛ ልጃችሁ ለስህተቱ ይቅርታን እየለመነ ይቅርታችሁን ብትነፍጉት ምን ያህል ህሊናውን እንደሚያቆስለው መገመት ከባድ አይደለም። ማንም ሰው በአለም ላይ ከሁሉ አስበልጦ ከሚቀርበው ሰው ይቅርታን እንደመነፈግ የሚያስጨንቀው እና የሚረብሸው ነገር አይኖርም። ለዚህ ነው እኛም ትላንት ለሰራነው ስህተት፤ ላጠፋነው ጥፋት፤ ለበደልነው በደል ከሌሎች ይቅርታ እኩል እራሳችንን ይቅር ማለት ሊለምድብን  የሚገባው። ለወቀሳ ሌሎች ሰዎች ከበቂ በላይ ናቸው፤ እኛም ከሌሎች ጋር ተደርበን እራሳችንን ብቸኛ አናድርገው።

አንዳንዶቻችን የሰራነው ጥፋት ለይቅርታ የሚከብድ እየመሰለን፤ በትላንት ስህተታችን ታስረን ዛሬንም ፤ ነገንም በጨለምተኝነት እናሳልፋለን። እኔ በበኩሌ ለይቅርታ የሚከብድ በደል ያለ አይመስለኝም። ምንም ያህል ስህተትን ብንሰራም፤ እስትንፋሳችን እስካለ ድረስ ከበደላችን በላይ ገዝፎ የሚታይ መልካም ስራ ለመስራት እድሉ አለን። አብዛኛዎቻችን ግን ለራሳችን ይቅርታ ስለምንነፍገው፤ መልካምነታችን እንዳያቆጠቁጥ አፈሩን በጸጸት እናደርቀዋለን። ጸጸት ከስህተት እስካረመን ድረስ መልካም ስሜት ነው፤ ነገር ግን ልኩን አልፎ ከንቱ ቢስነት እንዲሰማን ካደረገን ግን ጸጸት ሳይሆን ይቅርባይነትን መነፈግ ነው።

እስቲ አስቡት አንድ ሰው ትላንት ለሰራው ስህተት እስከመቼ ነው መወቀስ ያለበት? ይቅር አለመባልን በሌላው ላይ እራሱ ስናስበው ይከብዳል። ነገር ግን ባለማውቅ ሁላችንም እራሳችን ላይ የምንፈጽመው በደል ነው። በዚህ ምድር ላይ በይቅርታ የማይነጻ በደል፤ በንጹህ መጸጸት የማይታጠብ የልብ ቆሻሻ የለም። በትላንት ህይወታችን ምንም አይነት ሰው ብንሆንም፤ ዛሬን ነጽተን ለመኖር የሚያግደን አንዳችም ነገር የለም። በቅድሚያ ግን ከማንም  በፊት እኛ እራሳችን ይቅር ልንለው ይገባል።  መነሻችን ሳይሆን መድረሻችን ትርጉም እንዳለው መረዳት አለብን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን ሲሰቀል አብሮ በቀኝ  የተሰቀለው ፊያታዊ ዘየማን ምንም እንኳን እድሜውን በሙሉ በበደል እና በውንብድና ቢያሳልፍም፤ ነፍሱ ከስጋው እስክትላቀቅ ድረስ ለመልካም ምግባር ያልታደለ ቢሆንም፤ ለሞቱ ደቂቃ ሲቀረው በፈጣሪ ይቅር ባይነት ከማንም ቀድሞ ገነት ገብቷል። ይህንን ሚስጥር የሚረዳ ሰው እራሱን በጸጸት ከጥቅም ውጪ አያደርግም። ከንቱነት የሚሰማን ሁሌም እራሳችንን ከልክ በላይ ስለምንወቅሰው እና ይቅርታን ስለምንነፍገው ነው። የትላንት ቅሻሻችን ዘላለማችንን የማይለቅ ጠባሳ አድርገን ስለምንቆጥረው፤ ለመልካም ምግባር ያልታጨን አድርገን እራሳችንን እንቆጥራለን።

እውነቱን እናውራ ካልን፤ ሰዎች ከማይረባ ህይወት እራሳቸውን ለማላቀቅ ያስቡና አንዴ ተጨማልቄያለው በማለት ለራሳቸው ይቅርታን በመንፈግ ባሉበት ዘቅጠው ይቀራሉ። ለምሳሌ የቡናቤት ሴት መንፈሳዊ ሰው ለመሆን ብትፈልግ እንኳን፤ እራሷን ይቅር ማለት ይከብዳትና ለመልካም ስራ የማትበቃ እየመሰላት በጀመረችው የስህተት ጎዳና ትቀጥልበታለች። በመንፈሳዊውም ሆነ በአለማዊው መልኩ ብንቃኘው እራሳችንን ይቅር ማለት ከትላንት ስህተት እራሳችንን ለማላቀቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ሌሎች ሰዎች ይቅርታቸውን ቢነፍጉን እንኳን እኛ እራሳችንን ይቅር በማለት የህሊናን እረፍት ማግኘቱን መልመድ አለብን። ሰው የተናገረውን ቃል መልሶ ሊውጠው አይችልም፤ የሰራውን ስራ፤ ያጠፋውን ጥፋት ወደኋላ መልሶ ሊሰርዘው አይችልም። ብቸኛው ነገር በይቅርታ እራስን ማጽዳት ነው። ስለዚህ ሌሎች ይቅርታን ከነፈጉን የኛ ችግር ሊሆን አይችልም፤ በእርግጠኝነት የምናምነው ፈጣሪ ይቅር ይለናል፤ምክንያቱም  ይቅር ባይነት ባህሪው ስለሆነ። ከሌሎች ወቀሳ ለማምለጥ ብቻ አንሞክር፤ እረፍት የሚነሳው ትልቁ ወቀሳ የራሳችን የህሊና ጩኸት ነው።

ይቅርታ ለጠየቀን  ሁሉ ይቅርታችንን አንፈገው፤ ለራሳችንም ጭምር!!!ይቅርታ ለጠየቅ ይቅርታ ይደረግለት!!!

 

Do you have any comments?