አፍአዊ -ብኩን ቃል-አፍ ብቻ

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

“አፋዊ ሆንን፤ ሕያዊ ሳንሆን አፍአዊ ፤ ቃለ ህይወት ሳንሆን ብኩን ቃል-አፍ  ብቻ! እንጂ ቤታችን አንድ ነው”- ከሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን “እናት አለም ጠኑ” ከተሰኘው ተውኔት የተወሰደ   `

ቋንቋ እውነት መግባቢያ ነው! ነገር ግን ብቸኛው መግባቢያ እንዳልሆነ እርግጥ ነው። ይህንን ያስባለኝ ዛሬ አመሻሹ ላይ ያጋጠመኝ ነገር ነው። ሁሌም የኑሮ ልዩ ትርጉሞች፤ ተራ በሚመስሉ ነገሮች ውስጥ መገኘታቸው ይገርመኛል። እዚህ ቦታ ስመላለስ የመጀመሪያዬ አይደለም፤ በሳምንትም ሆነ በሁለት ሳምንት ለአንዳንድ ጉዳዮች እመጣለው። ዛሬም እንደልማዴ የተወሰኑ ወረቀቶችን ለማሳተም ነበር  እግር የጣለኝ። የመጣሁበትን ጉዳይ ፈጽሜ ወደሚከፈልበት ቦታ ስደርስ፤ ክፍያውን የሚቀበለው ሰው በፈገግታ ተቀበለኝ (ከዛሬ በፊት አይቼው አላውቅም ምንም እንኳን ደንበኛ ብሆንም) ። ፈገግታው የማስመሰል ሳይሆን፤ ከደስተኛነቱ የሚፈልቅ ጮራ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። የሚገርመው ደግሞ ሁለታችንን የሚያግባባን የጋራ ቋንቋ አለመኖሩ ነው። ፈግግታውን ሳይከድን በየመሃሉ የተወሰኑ ቃላቶችን ቢያወጣም፤ እውነቱን ለመናገር ምንም የሚለው ነገር አልገባኝም። ድንገት ፈገግታው ትክትክ ወዳለ ሳቅ ሲለውጥ፤ እኔም ሳቄን መቆጣጠር አላቻልኩምና አብረቅ መንተክተክ ጀመርን። የሚያስቀው እሱ የተናገረው ነገር ገብቶኝ የሳቅኩኝ መስሎታል። እውነቱ ግን በቋንቋ ሳይሆን፤ በስሜት ተግባብተን መሳቃችን ነው። ያለ ቋንቋ….አጭር ትዝታ፤ አጭር ደስታ!!!

ታድያ በመንገድ ላይ የተሾመ ምትኩን ዘፈን አስታወስኩት

“እኛ ግን በተግባባን ቁጥር እንጠፋፋለን

በተጠጋጋን ቁጥር እንራራቃለን

የቃላት ክምችት ኳኳታ ብቻ ነው….

ለዚህ ነው እንዳሸዋ ባህር በቋንቋ ችግር ተጥለቅልቀን

ሳንግባባ የቀረን………

ይህ የዘፈን ግጥም ከሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን “እናታለም ጠኑ ” ከተሰኘው ተውኔት የተወሰደ ይመስለኛል። ብዙዏቻችን አንድ አይነት ቋንቋ እያወራን አንግባባም። ምክንያቱም አፋዊ ብቻ ስለሆንን፤ ቃለ ህይወት ሳይሆን ብኩን ቃል- አፍ ብቻ ስለሆንን። መግባባት ቃላትን መለዋወጥ ብቻ አይደለም። እንደሱ ቢሆን ኖሮ ብዙ ሰዎች በሰላም በኖሩ ነበር። ብዙ ትዳሮች ከፍቺ በተረፉ ነበር፤ ብዙ ጓደኝነቶች ከመሰበር በዳኑ ነበር፤ ብዙ ፖለቲከኞች ለጋራ ጥቅም በሰሩ ነበር። ነገር ግን መግባባት ከቃላት መለዋወጥ የዘለለ ትርጉም አለው። ቋንቋ ብቸኛው መግባቢያ አይደለም፤ ሌላው መግባቢያ ምንድነው ካላችሁኝ ግን እኔም መለስ የለኝም……አፍአዊ መሆንን ስንተው ግን …እውነትም አንድ እንሆናለን።

ብኩን ቃላቶችን ማውራት ማናችንንም አያግባባንም። ልዩነቶች አለመጋባባቶች የሚሆኑት፤ ልዩነት ስለኖረ ሳይሆን፤ የቃላት ኳካታ ብቻ ስለሚሆኑ ነው። ሰዎች በአስተሳሰብ ቢለያዩ፤ በሃይማኖት ቢራራቁ፤ በዘር ቢከፋፈሉም አፍአዊ ካልሆኑ፤ ከቃላት ኳካታ ሲሸሹ ያለምንም ችግር ይግባባሉ። እኛ ግን የቃላት ኳካታ ብቻ ነን…..ለዚህ ነው እንደ አሸዋ ባህር በቋንቋ ችግር ተጥለቅልቀን ሳንግባባ የቀረን….እንጂ አንድ ነን!!!

One thought on “አፍአዊ -ብኩን ቃል-አፍ ብቻ

Do you have any comments?