መሪውን የጨበጠ ወዳሰኘው ይጓዛል

Posted on Posted in መነቃቂያ

እራሱን መጣል የሚፈልግ ሰው የለም። ሁላችንም እራሳችንን ለመጠበቅ የተቻለንን እናደርጋለን። ንጹህ ለመልበስ፤ ውበታችንን ለማቆየት፤ የምንበላውን ለማዘጋጀት፤ የለንም ከምንለው ጊዜ እንደምንም ብለን ለመሻማት እንሞክራለን። ለውጫዊ ማንነታችን የተቻለንን ጊዜ፤ የተቻለንን ገንዘብ መስዋት እናደርጋለን። ችግሩ ግን የህይወታችን መሰረቱ የውጫዊ ማንነታችን አለመሆኑ ነው። ትልቁን አትኩሮት እና እንክብካቤ የሚሻው ውጫዊው አካላችን ሳይሆን ውስጣዊው ማንነታችን ነው።

አሁን ላለንበት ሁኔታም ሆነ ለመረጥነው የህይወት ጎዳና ትልቁን ድርሻ የሚይዘው አይምሮዋችን ነው። ይህ በቅድሚያ ከምንም ነገር በላይ ማመን ያለብን እውነታ ነው (ይህንን ማመን የተሳነው ሰው፤ ቀሪው ነገር ትርጉም አይሰጠውም)። ይህንን እውነታ በቅጡ መረዳት ከቻልን፤ ኑሮዋችንን ለሚመራው አይምሮዋችን የምንሰጠውን አነስተኛ ጊዜ እንታዘባለን። አንድ መኪና ያለሹፌር ሞተሩ ተነስቶ ቢለቀቅ፤ በርግጠኝነት ቀጥ ብሎ ለመጓዝ አይቻለውም። የመኪና መሪ እንደዘበት ያለ አትኩሮት የሚተው አይደለም። መኪናው ካሰበበት ቦታ ለመድረስም ሆነ ከአደጋ ለመጠብቅ መሪው በደህና ሹፌር እጅ መውደቅ አለበት። ሊረጋገጥ የሚገባው ነገር የተሳፋሪው ምንነት ሳይሆን የሹፌሩ ችሎታ ነው። አይምሮዋችንም ከዚህ አይለይም፤ ያለ ብቁ ሹፌር ከለቀቅነው፤ ካገኘው ጋር እየተጋጨ፤ ወደፈለግነው ሳይሆን መንገዱ ወደመራው አላማ ቢስ ጎዳና ይነዳናል።

በዚህ ዘመን ጭንቀት እና ግራ መጋባት እጅግ የተለመዱ ነገሮች ናቸው። አላማ የሌላቸው፤ ወዴት እንደሚሄዱ የማያውቁ ፤ ቢያንስ የሚፈልጉትን የማያውቁ ወጣቶችን መመልከት አዲስ እና የሚያስገርም ነገር አይደለም። በጉም ውስጥ የምንጓዝ፤ ንጹህ የሆነ እይታ የጎደለን ጥቂቶች አይደለንም። የዚህ ሁሉ ችግር መንስዔ ታዲያ፤ የህይወታችንን መሪ ለጨበጠው ለአይምሮዋችን የምንሰጠው አነስተኛ አትኩሮት ነው። የምናስገባቸው እውቀቶች፤ የምናምናቸው እምነቶች፤ የምንከተለላቸው ትዕዛዛቶች ውስጥ  መርጠን ከያዝናቸው ይልቅ፤ በደመነፍስ ያግበሰበስናቸው በይዘት ይበልጣሉ።

እንዲህ አይነት ሃሳብ ሲነሳ በብዙዎች አይምሮ ውስጥ የሚያቃጭል አንድ ማስተባበያ አለ “አስተዳደግ፤ ወይም ማህበረስብ ያወረሰኝን ለመቀየር በጣም ከባድ ነው” የሚል ማስተባበያ።እርግጥ ቤተሰቦቻን አልያም ማህበረሰቦቻች ለህይወታችን መሰረት ቢጥሉልን መልካም በሆነ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ሰው ለዚህ አልታደለም። ለውድቀታችን ወይም የማንፈልገውን ኑሮ ለመምራታችን ሌሎችን እንደምክንያት መውሰድ የተሸናፊዎች የጨዋታ ስልት ነው። አንድ ሰው ነፍስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ፤ የህይወቱን መሪ የመጨበጥ መብቱ የተጠበቀ ነው። በቤተስብ፤ በማህበረሰብ፤ በጓደኛ ተጽዕኖ መጓዙን ከጠላው፤በሹፌሩ ቦታ እራሱን አስቀምጦ ወዳሰኘው ጎዳና መጓዝ ይችላል። ይህ መንገድ የሚጀመረው ታዲያ በእምነት ነው። የእምነት ዋናው ጥበብ “እንዴት ይሆናል?” የሚለውን አደናቃፊ ጥያቄ እንድናልፍ ማገዙ ነው።

ከላይ ወዳነሳነው ሃሳብ ስንመለስ፤ ግራ መጋባት እና የሚፈልጉትን አለማወቅ በብዙ ሰዎች ላይ የሚታየው ለምንድን ነው ብለን ብንጠይቅ፤ መልሱ አይምሮዋችንን ለመገንባት ጊዜ ባለመስጠታችን ነው። እውቀት መጨመሩ ቢከብደን እንኳን፤ የማይጠቅሙንን አስተሳሰቦች ለማስወገድ በቂ ጊዜ ለራሳችን ሊኖረን ይገባል። ህይወታችን በሙሉ የሚመራው በአስተሳሰባችን ነው። ብዙ ተመራማሪዎችም ሆኑ ሊቃውንቶች በተለያዩ ሃሳቦች ላይ መስማማት ቢያቅታቸውም እንኳን፤ በዚህ መሰረታዊ ህግ ላይ ይስማማሉ። ለምሳሌ

ታላቁ የስነ ልቦና ተመራማሪ ዶ/ር ኖርማን ቪንሰንት ፒል ይህንን ብሏል “Change your thoughts and you change your world”

የቡድሂስት እምነት መስራች ቡዳህ ” we are shaped by our thoughts; we become what we thinks. when the mind is pure joy follows like a shadow that never leaves”

ኮንፊውሺየስ በበኩሉ እንዲህ ብሏል ” The more man meditates upon good thoughts; the better will be his wolrd and the world at large”

እኒህ ከላይ የሰፈሩት ለምሳሌ ያህል የጠቀስኳቸው ናቸው እንጂ፤ ሌሎች ይህንን ሀሳብ የሚደግፉ፤ የሚያረጋግጡ ጽሁፎችን ማቅረብ ይቻላል። ታዲያ አስተሳሰባችን በህይወታችን ላይ ይህንን ያህል ተጽዕኖ ካለው፤ አይምሮዋችንን ለመፈተሽ ጊዜ ማጣቱ ተገቢ ነው? ኸርል ናይቲንጌል የሰው ልጅ በቀን ቢያንስ አንድ ሰዓት እራሱን ለመፈተሽ ወይም አላማ ላለው ስራ ቢያውል በአምስት አመታት ውስጥ ካሰበበት ቦታ ለመደርስ የሚያግደው ነገር እንደሌለ አስረድቷል። ቢያንስ በቀን አንድ ሰዓት እራሳችንን ለመፈተሽ ካዋልን፤ የምነፈልገውን ማንነት እና ህይወት ከመያዝ የሚያግደን ምንም  ነገር አይኖርም። ከግራ መጋባት ወጥተን የምንፈልገውን ለማወቅ መሰረቱ እራስን መፈተሽ፤ አይምሮን ማጎልበት ነው። እግረ መንገዱን ፤ባህሪን ለመለወጥ እንደመነሻ ከሚያገለግሉት ነገሮች ውስጥ የሚከተሉትን መሞከር ይቻላል

– ማንነትን ገንቢ የሆኑ መጻህፍትን ማንበብ

-ሜዲቴሽን (ጥሞና)

-መንፈሳዊ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ

-አካላዊ እንቅስቃሴ ወይም ስፖርት መስራት

-ለብቻ ከራስ ጋር ጊዜን ማሳለፍ

One thought on “መሪውን የጨበጠ ወዳሰኘው ይጓዛል

  1. አመሰግናለው እይወቴን በእጅጉ እንድመራ እና ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረኝ አድርጋቹኛል ከዚህም በላይ ብዙ እጠብቃለው በርቱልኝ

Do you have any comments?