ባገኘኸው ቦታ ብቀል…..

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

grow where u can

ይህች አበባ ከቤቴ በራፍ ላይ ያለች አበባ (አበባ መሳይ ቅጠል) ናት። ዘወትር ደረጃውን ስውጣም ሆነ ስወርድ እንዳልረግጣት እጠነቀቃለው። ጥንቃቄዬ የመጣው ግን ከብዙ ጊዜ በኋላ በተለየ አይን ስለተመለከትኳት ነው። አንድ ቀን በሬን ቆልፌ ወደታች ስወርድ፤ ድንገት ቁልፌ ከመሬቱ ላይ ወደቀ። ቁልፌ ወድቆ ያረፈው፤ ከዚህች ትንሽ አበባ መሳይ ቅጠል ጎን ነበር። ቁልፌን ከማንሳቴ በፊት፤ ይህችን ቅጠል አስተውዬ ተመለከትኳት። ዙሪያዋን በድንጋይ የተከበበች፤ ብቸኛ ነፍስ። አፍር ለአይን በማይታይበት፤ ድንጋይ ላይ፤ ያገኘችው የስንጥር ያህል ቀዳዳ ተጠቅማ በድፍረት የበቀለች ህይወት መሆኗን አስተዋልኩኝ። እንደልቤ አፈር ካላገኘው አልበቅልም ብላ ያላመጸችውን ይህችን ቅጠል ሳይ፤ መንፈሴ እንደልማዱ አፈንግጦ ሌላ ነገር ማሰብ ጀመረ።

ብዙዎቻችን ለህይወታችን መሰናከል፤ ዙሪያችንን መውቀሱ ይቀናናል። ለህይወታችን መበላሸት፤ ለውድቀታችን ሌላው ላይ እጣታችን መቀሰሩ የተለመደ መልሳችን ነው። ነፍስ ዘርተን ለመብቀል፤ ዙሪያው በሙሉ አፈር እንዲሆን እንሻለን። ህይወትን አጣጥመን ለመኖር፤ ዙሪያችን ሁሉ መልካም እስኪሆን እንጠብቃለን። በቤተሰብ ጥፋት፤ በማህበረሰብ ስህተት፤ በሃገር ውድቀት፤ ዙሪያው ድንጋይ ነው ብለን ሳንበቅል እንቀራለን። ምንም እንኳን መብቀያ ቦታ ብናገኝም፤ በዙሪያችን ነፍስ ስላላየን የማይቻል ይመስለናል። ለዚህ ነው ይህች አበባ፤ ያላሰብኩትን ያሳሰበችኝ። እኔ በተፈጥሮ አምናለው፤ የሰው ልጅ አይኖቹን ከፈቶ ማየት ከቻለ፤ ከተፈጥሮ የላቀ መምህር ያለም አይመስለኝም። ተሳስቼ ሊሆንም ይችላል።

በእድል የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ፤ እድል ሁሌም ዝግጁ ሆኖ ለሚጠብቅ የምትሰጥ ሙሽራ ናት። የእድል እውነተኛ “ትርጉም ጥረት ከአጋጣሚ ጋር ሲገናኝ” የሚል ነው። ማንም ሰው እጅ እና እግሩን አጣጥፎ እድልን ቢጠብቅ፤ በእድሜው እያሾፈ ነው። እድለኛ የምንላቸው ሰዎች፤አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ተዘጋጅተው የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው።

ማድረግ የምትፈልገው ነገር ካልህ፤ ትክክለኛው ሰዓት እስኪመጣ ብለህ አትዘናጋ። በህይወት ውስጥ ትክክለኛዋ ሰዓት የአሁኗ ደቂቃ ብቻ ናት። ሁኔታዎች እስኪመቻቹ መጠበቅ፤ አሁን ያለህን አጋጣሚዎች ማባከን ነው። ለዚህ ነው ይህችን በደጃፌ ፤ ከደንጋዮቹ መሃከል የስንጥር ያህል ቦታ ላይ የበቀለችው አበባ ዘወትር የምቃኛት፤ ባየትኋት ቁጥርም ለራሴ እንዲህ እያልኩኝ እነግረዋለው “ለወቀሳ ጊዜ አልሰጥም፤ በገኘሁት ቦታ እበቅላለው፤ ባለችኝ አፈር ላይ አብባለው”

ያለህ ከበቂ በላይ ነው፤ ምንም የሌለህ የሚመስልህ፤ አሳብህ እና ጭንቀትህ በሌሉህ ነገሮች ላይ ስለሆነ ብቻ ነው።

Do you have any comments?