በሰው ተስፋ አትቁረጥ

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

You must not lose faith in humanity. Humanity is an ocean; if a few drops of the ocean are dirty, the ocean does not become dirty”Mahtama Gandih

ምናልባት ሰዎች በድለውህ፤ አልያም አስከፍተውህ ሊሆን ይችላል። ማን ያውቃል ያመንከው ከድቶህ፤ የጠበቅከው እረስቶህ፤ ተስፋ የጣልክበት ጥሎህ ሊሆንም ይችላል። ወይም ደግሞ የእለቱን ዜና ስትሰማ፤ ሰው በሰው ሲጨክን ስታይ እውነት መልካም ሰዎች ይኖሩ ይሆን ብለኽ አስበህ ሊሆንም ይችላል። ማን ያውቃል ከልብህ ወደህ ልብህን የሰጠኸው ሰው፤ ልብህን የጣለበት ጠፍቶት ሌላ መውደጃ ልብ አጥተኽ ይሆናል።

በእለት ተእለት ኑሮዋችን የመገናኛ ብዙሃን የሚያሰሙን ዜናዎች፤ እውነትም በሰው ልጅ ተስፋ እንድንቆረጥ ያደርገናል። መልካም ሰዎች እና ምግባሮቻቸው እየመነመኑ የመጡ ይመስለንና እራሳችንን ከማህበረሰቡ እየነጠልን እንመጣለን።

ሰው ለመውደድ ሁለቴ እናስባለን፤ ልባችንን እንዳይሰበር በመስጋት። ደግ ለመስራት ግራ ቀኙን እናያለን፤ በበጎነታችን እንዳንጎዳ በማሰብ። ሰው ማመን ፈተና ሆነብን። በዚህ መሃከል ግን መልካም ሰዎች እያሉ እንደሌሉ ተቆጠሩ። የክፋት ወሬ አለምን ሲያዳርስ፤ መልካም ዜና ግን ከቤት አልፎ ጎረቤት መሰማት አቃታት።

በሰው ልጅ ተስፋ መቁረጥ ያለብን አይመስለኝም። አንዴ ስለተከዳን ሁሉም ሰዎች ከሃዲዎች ናቸው ብለን መደምደም የለብንም። መጥፎ ዜናዎች ከፍ ብለው ስለተሰሙ፤ መልካም ስራ የለም እያልን በሰብዓዊነት ላይ ተስፋ ባንቆርጥ መልካም ነው። አለም ልክ እንደ ውቂያኖስ ናት፤ ጥቂት የክፉ ሰዎች ጠብታ ስላለባት ብቻ ውቂያኖሱ ተበክሏል ብለህ ተስፋ አትቁረጥ።ደግመህ ለመውደድ አትፍራ፤ ደግመህ ይቅር ለማለት አትስጋ፤ የዋህ መሆንህን አትጥላው።አለምን በርቀስ አርገን ብናያት፤ ማመን ከሚከብደን በላይ መልካም ሰዎች አሏትና።

“አለም ልክ እንደ ውቂያኖስ ናት፤ ጥቂት የክፉ ሰዎች ጠብታ ስላለባት ብቻ ውቂያኖሱ ተበክሏል ብለህ፤ ተስፋ አትቆረጥ።”

 

 

 

Do you have any comments?