እንዴት መታወስ ትፈልጋለህ?

Posted on Posted in መነቃቂያ

አንድ ጊዜ አንድ ሰው የጠዋቱን ጋዜጣ ሲያነብ፤ በስህተት የወጣ አንድ አስደንጋጭ ዜናን ይመለከታል። ዜናው ስለራሱ የተዘገበ ነበር። ዘጋቢዎቹ በስህተት የወንድሙን ሞት እሱ እንደሞተ አድርገው ነበር የዘገቡት። የዜናው አርስትም  “የድማሚቱ ንጉስ አረፈ” ይልና “ይህ ሰው የሞት ነጋዴ ነበር” ሲል ያትታል። ይህ ሰው የዳናማይት (ድማሚት) ፈጣሪ አልፍሬድ ኖቤል ነበር። ወንድሙ ሲሞት እሱ የሞተ መስሏቸው ነበር ዜናው በጋዜጣ ያሰራጩት። አልፍሬድ መጀመሪያ ዜናውን ሲያየው እጅግ ደንግጦ ነበር፤ ቀልቡን ሲገዛ ግን “የእውነት ይህችን አለም ስሰናበት ሰዎችን በዚህ ነው የሚያስታውሱኝ” ሲል አሰበ። ከዛን እለት ጀምሮ ህይወቱ ተለወጠች፤ የሞት ነጋዴ ተብሎ መታወስን ስለጠላ፤ በመልካም ነገር የሚታወስበትን ነገር ፈጠረ።  ቀሪውን ህይወቱንም ለሰላም አዋለው። አላማው ተሳክቶም ዛሬ አልፍሬድ ኖቤል “የኖቤል ሽልማት” በተሰኘው መልካም ስራው አለም ሁሉ ያስታውሰዋል። ማን ነው ዛሬ ኖቤል ሲባል ድማሚት ትዝ የሚለው? ማንም! ኖቤል ሲባል ሰላም ትዝ ይለናል እንጂ።

መቼም ዘላለም የሚኖር የለም።ህይወት ማለት በውልደት እና በሞት መካከል ያለችው አጭር ጊዜ ናት። ከየት እንደመጣን እንደማናውቅ ሁሉ ወዴት እንደምንሄድም በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። ምንም እንኳን ሁሉም ሰው ወደ መቃብር መሄዱ ባይቀርም፤ አሟሟታችን ግን አንድ አይነት ነው ብዬ አላምንም። አንዳንዶች ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመውበት፤ ያለጸጸት ወደሌላኛው አለም ሲሸጋገሩ ብዙዎች ደግሞ ጊዜው እንዳጠረበት ሰው፤ ያሰቡትን ሳያሳኩ እንደተንቀዠቀዡ፤አንድ ቀን ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ከመቃብር ጉድጓዳቸው ደጃፍ ይገኛሉ። እንደኔ ሰው መልካም ኑሮ ኖሮ ሞተ የሚባለው፤ በመልካም ነገር መታውስ ሲችል ነው። ግዴታ አለም ሁሉ ሊያውቀን አይገባም፤ ልጆቻችን መልካም ወላጅ ነበረኝ ብለው ሲያስታውሱን፤ ወንድም እህቶቻችን መልካም ወንድም መልካም እህት ነበረኝ ብለው ሲያስታውሱን፤ ወላጆቻችን መልካም ልጅ ነበረኝ ብለው ሲያስታውሱን፤ እውነትም ህይውታችን ትርጉም ነበረው ማለት ነው። ከእኛ በፊት እኛን የመሰለ ማንም አልነበረም፤ ነገም እኛን የሚመስል ማንም አይፈጥርም፤ ስለዚህ የራስህ አሻራ እንዴት አድረገህ እንደምታኖር አስብበት።  life time

Do you have any comments?