ብቸኛዋ ፍቅር

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

አንድ ጊዜ የሰው ልጅ ስሜቶች ሁሉ ተሰብስበው ለሽርሽር ወደ አንድ ደሴት ይሄዳሉ። እንደየባህሪያቸው ሁሉም መልካም ጊዜን እያሳለፉ ነበር። ድንገት ግን ሃይለኛ ማዕበል ተነሶቶ ደስታቸውን አደፈረሰባቸው። ቶሎ ብለውም ደሴቱን መልቀቅ እንዳለባቸው አዋጅ ተላለፈ።  እያንዳንዳቸውም ስራቸውን አቋርጠው ወደየ ጀልባቸው እሩጫ ጀመሩ።

ሁሉም ስሜቶች እራሳቸውን ለማዳን ሲሮጡ፤ ፍቅር ግን ቶሎ ለመሸሽ አልፈለግችም ነበር። ብዙ የምትሰራው ነበራትና በደሴቱ ላይ ስትንገዋለል፤ መሸ። የጨረቃን መሸሽ ስታይ፤ ፍቅር ከደሴቱ መውጫ ሰዓቱ እንደደረሰ ተረዳች፤ ነገር ግን ሁሉም ጀልባዎች ሌሎች ስሜቶችን ጭነው ሄደዋል። በተስፋ ዙሪያዋን ቃኘች ማንም የሚያድናት አልነበረም።

ድንገት ሃብት በሚያምር ጀልባ ደሴቱን ሲያቋርጥ ተመለከተችና ” ሃብት፤ እባክህ በጀልባህ ውሰደኝ?” ብላ ጮኸች። ሃብት ግን እንዲህ ሲል መለሰላት ” አልችልም፤ ጀልባዬ በወርቅ እና በብር ሞልቷል ለአንቺ የሚሆን ምንም ቦታ የለኝም” አላት።

ትንሽ ቆይቶ ትዕቢት በሚያምር ጀልባው ደሴቷን እያቋረጠ አየችው፤ ይሄኔ ፍቅር ተጣራች ” ትዕቢት ሆይ፤ በዚህ ደሴት ብቻዬን ነኝ፤ ከዚህ የሚወስደኝ እፈልጋለው፤ እባክህ በጀልባህ ጫነኝ” ስትል ተማጸነችው። ትዕቢት ግን መልሶ እንዲህ አላት “አልችልም፤ የጫማሽ ጭቃ፤ ጀልባዬን ያቆሽሽብኛል” ብሎ ጥሏት ሄደ።

ቀጥሎ ሃዘን በጀልባ ሲያልፍ፤ ፍቅር እንደገና ተጣራች ” ሃዘን ሆይ እባክህ በጀልባህ ጫነኝ” አለችው። ሃዘንም እንዲህ አላት “ይቀርታ በጣም ሃዘን ላይ ስለሆንኩ ብቻዬን መሆን እፈልጋለው።” ብሎ ሳይጭናት ጥሏት ሄደ።

ከዛ ደስታ ደሴቱን ልታቋርጥ መጣች፤ ፍቅር አሁንም ለእርዳታ ተጣራች። ደስታ ግን በደስታ እየተፍለቀለቀች ስለነበር ፍቅርን ጭራሽ ሳታያት አለፈች። ፍቅር ግራ ገባት፤ የሚረዳት የለምና ተጨነቀች። ድንገት ከየት እንደመጣ የማታውቀ ድምጽ ስሟን ጠራት “ፍቅር…ነይ እኔ በጀልባዬ ጭኜ እወስድሻለው” አላት። ጀልባውንም አቆሞ ፍቅርን ጫናት። ጀልባው ውስጥ ስትገባ እውቀትን ተቀምጦ አገኘችው። ፍቅር ግራ ገብቷት  “እውቀት ሆይ፤ በደግነት ይህንን ጀልባ አስቁሞ ከሃዘን ያወጣኝ ማን እንደሆነ ታውቃለህ?” ብላ ጠየቀችው።

እውቀትም መልሶ “አዎ፤ ጀልባውን ያቆመለሽ ጊዜ ነው” አላት

ፍቅርም ” ጊዜ ለምን እንዲህ ደግ ሆነልኝ?” ስትል መልሳ ጠየቀች።

“ምክንያቱም የፍቅርን ዋጋ የሚያውቀው ጊዜ ብቻ ስለሆነ። ፍቅር ደስታን እና ሰላምን እንደምታመጣ ጊዜ ያውቃል።” ሲል መለሰላት።

በሃዘን ጊዜ ፍቅርን እናሸሻሻታለን፤ ደስ ሲለን ደግሞ ጨርሰን አናያትም፤ ሃብት ሲኖረን ለፍቅር ቦታ ይጠበናል፤ እራሳችንን ያለመጠን ስንወድ ለፍቅር ጎንበስ ማለቱ ይከብደናል። የፍቅር ደጅ ጥናት ትንሽ አልበዛም? ፍቅርን የሚጭን ጀልባ እንዲህ ይጥፋ?

(Author Unknown; i just feel like it is an interesting story to share; that is why i translated it to Amharic)

 

Do you have any comments?