መፈራረቅ

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

“Opposites follow each other as night follows day; try to cling to one or the other and you will be disappointed by your failure; let the way do its dance; be the dance of reconciliation of opposites.” Lao Tzu from the Dao de Ching

ይህች አለም በተቃርኖ የተሞላች ነች፤ ለብርሃን ጨለማ፤ ለክረምት በጋ፤ ለብርድ ሙቀት፤ ለሃዘን ደስታ፤ ለውድቀት ስኬት የተጣመሩባት መንትያ አለም። የኛም አኗኗር በተቃርኖ ላይ አንጻራዊ በሆነ መልኩ የተመሰረተ ነው። በህይወታችን የሚገጥሙን ነገሮች ሁሉ በግልባጭ ሌላ መልክ አላቸው። ሆኖም አንዳንዴ ይህንን ሃቅ ቸል እንለዋለን። ቸል ማለት ስል፤ አዘውትረን ስለማንተገብረው የአለምን ተቃርኖ ረስተን አንድ ነገር ላይ ሙጥኝ ስንል፤ ሌላኛው ገጽታ ሲከሰት ደስተኛ መሆን ያቅተናል።ምክንያቱም ሁሉም ነገር እንደነብረው ሆኖ መቅረት ስለማይችል። ምንም አይነት የህይወት አጋጣሚዎች ተቃራኒ ገጽታ እንዳላቸው እና እንደሚፈራረቁ ማመን አለብን።

ለምሳሌ ደስተኛ በሆንን ጊዜ የደስታን ተቃራኒ ሃዘንን እንዘነጋዋለን፤ መቼም ተቃራኒ ነገሮች መፈራረቃቸው አይቀርምና ሃዘን ሲጎበኘን ለመቋቋም ይከብደናል። ከዛ ደግሞ ሃዘን ላይ ሙጥኝ እንልና ደስታን እንረሳዋለን፤ መፈራረቃቸው አይቀርምና ደስታ በጊዜው ሃዘንን ሲተካ ያልጠበቅነው ስለሆነ እምብዛም ስሜት አይሰጠንም። ስናገኝ ማጣት እንደሚመጣ መዘንጋት የለብንም፤ ያለንን ስናጣ ቅስማችን እንዳይሰበር። ስንቸገር ማግኘት እንዳለ ለልባችን እንንገረው፤ ዉሎ ለማደር ጉልበት እንዲያገኝ።

የአለምን የተቃርኖ ሚስጥር መረዳት ማለት፤ አሉታዊ አስተሳስብ መያዝ አይደለም። ይልቁንም እኛነታችን በቁሳዊ ነገሮች ወይም ከኛ ውጪ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዳይንጠለጠል ይረዳናል። እጽዋት ለምን ክረምት ወደ በጋ ተለወጠ ብለው አይከፋቸውም፤ አሳዎች ለምን ሞገዱ  ተነሳ ብለው ከተፈጥሮ አይሟገቱም፤ ወንዞች አንዴ ሲሞሉ ሌላ ጊዜ ሲጎድሉ አያማርሩም። ምንም እንኳን ለኛ ለሰዎች ቢከብደንም፤ አኗኗራችን የሚቀይረው አስተሳሰብ ግን ይህ ነው። ሁሉም ነገር እስከመጨረሻው አይቆይም። ምን አልባት አሁን በመከራ ውስጥ ልትሆን ትችላለህ፤ በእርግጠኝነት ግን መከራህ በደስታ መቀየሩ አይቀርም፤ ዛሬ ኪስህ ባይሞላ ማጣት በማግኘት እንደሚተካ እመን። ዛሬ ሁሉ የሞላልህ ከሆንክ ደግሞ፤ አንትህን ከንብረትህ ለየው ምክንያቱም ምንም ቋሚ ነገር የለምና፤ ይህንን ካሰብክ ማጣት ሲጎበኝህ ሰማይ አይደፋብህም። ዛሬ የተቀመጥክበት ወንበር ነገ ለሌላው ይሰጣል፤ በወጣህበት መሰላል መወረድህ ግድ ነው። ሁሉም የህይወት ልምድ ተቃራኒ ገጽታ አለው እና። የነገሮች መፈራረቅ እስከ አለም ፈጻሜ ድረስ ይኖራል።

ከዚህ የአኗኗር ዘይቤ ጋር እራሳችንን እንዴት እናዋህደው?

መልሱ- ስሜታችንን በውጫዊ ነገሮች ላይ ማንጠልጠሉን እናቁም። ወደ ውስጣችን እንመልከት። ወደ ውስጡ የሚመለከት ሰው በዙሪያው የሚከናወነው ግርግር እምዛም አይረብሸውም።ደስታ ከውስጥ የምትፈልቅ በተፈጥሮ የምትገኝ የማትነጥፍ ወንዝ ናት። ይህቺን ወንዝ አንዴ ቆፍረን ካገኘን፤ በዙሪያችን ያለው ወንዝ ቢደርቅ እኛ በጥም አንሞትም። መጽሃፉም “ሁሉም ነገር ከንቱ ነው የከንቱም ከንቱ ነፋስን እንደመከተል ነው” ያለው እኔ እንደሚመስለኝ ሁሉም ነገር ማብቂያ እንዳለው ሊያመላክተን ነው። ህይወት መንገዷን በቀየረች ቁጥር አንደናገጥ፤ መለወጥ የምንችለውን ነገር ለመለወጥ እንሞክር፤ ከዛ የዘለለው ግን መፈራረቁ አይቀርም። ይህ የተፈጥሮ ህግ ነውና።

 

 

 

 

 

 

 

Do you have any comments?