በኑሮ ቅርንጫፍ ላይ የተንጠለጠልን ቅጠሎች!!!

Posted on Posted in መነቃቂያ

እስቲ ከልብ እናውራ….. እዳ ሆኖበት መቼም የሰው ልጅ ስኬቱን የሚለካው፤ ህይወቱ ለራሱ በምትሰጠው ደስታ እና እርካታ ሳይሆን፤ በሌሎች ዘንድ በሚበረከትለት ተቀባይነት እና በሚደፋው ሚዛን ነው። እኔም በግሌ ከዚህ ወጥመድ ላመልጥ አልቻልኩም ነበር። ስህተቱን የሚናገር ሰው ለለውጥ እራሱን ያዘጋጀ ነውና፤ እኔም ስለራሴ ስህተት እናገራለው። ለራሴ የነፈግኩት ትኩረት ይቆጨኛል፤ በልቤ ውስጥ ታንሾካሹክ የነበረችውን  ነፍሴን ችላ ብዬ፤ ትርጉሙ የማይገባኝን የሌላውን ጩኸት ለመስማት ስሞክር ብዙ አመታትን አቃጥያለው።  ዛሬም ይህንን አጉል ልምድ ገንጥለን ለመጣል ብዙዎቻችን እንሞክራለን፤ ግን ቀላል መንገድ አይደለም። ምክንያቱም `እራሳችንን ከሌላው ሰው ጋር ማፎካከሩ፤ ሳይታውቀን በላይችን የበቀለ፤ ስሩ እጅግ ስር የሰደደ መራራ ዛፍ ነው።

በአንድ ትምህርታዊ ቪዲዮ ላይ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ሰምቼ ነበር “እራስን ከሰው ጋር ማፎካከር ማለት፤ ድመት የራሷን ጭራ ለመያዝ ከምታድረገው ጨዋታ ጋር ይመሳሰላል”። ይህንን ሳስብ እራሴን እንዲህ ብዬ ጠይቅኩት፤ ህይወቴን ከሌላ ሰው ጋር ባላፎካክር፤ እራሴን በምን አይን እመለከተው ነበር? ገምጋሚ ባይኖረኝ ለኔ ስኬት ምን ነበር? ተመልካች ባይኖረኝ ኑሮዬ ምን ይመስል ነበር? ጠያቂ ባይኖረኝ ምን ማወቅ እፈልግ ነበር? መዛኝ ባይኖረኝ ልኬ ምን ይሆን ነበር? መልሱን ባውቀውም ለራሴ ልመስልሰው ግን አልደፈርኩም። ምክንያቱም  ሃቁን መዋጡ ከብዶኝ። ብዙዎቻችን ሌላው ባሰመረልን ልክ ለመዝለል ስንሞክር ጉልበታችን ሳንኖርብት ይደክማል።

ጥቂቶች ግን ምን ያህል እድለኞች ናቸው? እንደጉድ የሚጮኸውን የሌላውን ኳኳታ ችላ ብለው ፤ ሹክ የምትለውን የነፍሳቸውን ጥሪ መስማት የተቻላቸው እንዴት ያስቀናሉ? በራሳቸው መንገድ ለመኖር ሲሉ ሌላው ባወጣው መስፈርት ለመውደቅ የወሰኑ። በጎረቤታቸው ጸሃይ የጎጇቸውን ጭላጭል አትሸማቀቅም። ምክንያቱም ህይወታቸውን ከሌላ ሰው ጋር ስለማያፎካክሩ። ነፍሳቸው በራስዋ ምሉዕ ስለሆነች፤ እውነተኛ ማንነታቸውን ስላገኙ ህይወታቸው ለምትሰጣቸው እርካታ የሌላውን ሰው ማረጋገጫ አይሹም። ግን ይህንን ማድረግ ለብዙዎቻችን  ለምን ከበደን?

ይህንን በደንብ የሚይሰረዳ አንድ ምሳሌ ላጫውታችሁ። ላዎ ትዙ ( LAO TZU) ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረ ሰው ነው (በእውነት ምድር ላይ መኖሩን የሚጠራጠሩ አሉ፤ Mythical ወይም በአፈ ታሪክ ብቻ የነበረ ነው የሚሉ ማለት ነው) ። ይህ ሰው ከመጽሃፍ ቅዱስ ቀጥሎ በምድር ላይ በመተርጎም ሁለተኛ የሆነ ድንቅ ጽሁፍ አበርክቶልን አልፏል (ምን አልባት ደጋግሜ ከዚህ መጽሃፍ ጥቅሶችን ብጠቅስ አትታዘቡኝ፤ ድንቅ ስለሆነ ነው)። እናም እራሳችንን ከሰው ጋር የማፎካከሩን አባዜ ማስውገድ  ከፈለግን፤ ላዎ ትዙ እራሳችንን እንደሚከተለው፤ ልዩ በሆነ መንገድ መመልከት አለብን  ይለናል……እነሆ….

” ህይወት ብዙ ቅርንጫፍ እንዳለው ዛፍ ናት። በቅርንጫፉ ላይ ያሉት ቅጠሎች ሁሉ ልዩ ናቸው፤ ሁሉም ቅጠሎች ከዛፉ ስር ጋር በተለያየ መንገድ ነው የሚገናኙት፤ አንዳቸውም ቢሆንም ተመሳሳይ መንገድ የላቸውም። ዛፉ ሁሉንም ቅጠል እና ቅርንጫፍ ሳያዳላ ይደግፋቸዋል፤ ነገር ግን አንዱ ቅጠል ለሌላው ቅጠል እንግዳ ነው። አንዳቸውም ቅጠል ሌላውን ቅጠል ለመምሰል አይጥሩም።አይቀናኑም፤ አንዱ ቅጠል ከሌላው  ቅጠል አንሳለውም ፤ እበልጣለውም ብሎ እራሱን አያስጨንቅም። አንዱ ቅጠል ከስሩ ጋር በሚገናኝበት መንገድ፤ ሌላው ልሂድበት ብሎ እራሱን አይሞግትም። ይልቅ እደተፈጥሮው እራሱን ሆኖ ይኖራል እንጂ። ሁሉም ቅጠሎች ሳይፎካከሩ እንደተፈጥሯቸው ይኖራሉ” ጸሃፊው በዛፍ እና በቅጠል የነገረን ምሳሌ የሰው ልጅ ህይወት ነጸብራቅ ነው፤ ማለትም የሰው ልጅ እውነተኛ አኗኗሩ መሆን የነበረበት!

ደስ የሚል አገላለጽ አይደለም? ሁላችንም በኑሮ ላይ የተንጠለጠልን ቅጠሎች ነን፤ ከስሩ ጋር ለመገናኘት እና ለመኖር  የየራሳችን መንገድ የተበጀልን። ምን ዋጋ አለው….. እራሳችንን ከሰው ጋር ስናፎካክር፤ ከስሩ ጋር የሚያገናኘንን መስመር ትተን ሌላው ቅጠል ባረፈበት ለማረፍ ስንጥር በጊዜ እንጠወልጋለን። ልዩነትቻንን መቀበል ተስኖን፤ ነፋሳችንን አቀጨጭናት። ከዚህ በላይ ኑሮዋችንን ግልጥ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ ምን አለ?

እናም ድንገት ነፈሳችሁ ስታፈነግጥ ፤ አይናችሁ ከሌላው ጓዳ ሲቀላውጥ፤ ለራሳችሁ ይህንን አስታውሱት፤ ሁላችንም በኑሮ ቅርንጫፍ ላይ የተንጠለጠልን ቅጠል ነን፤ ሌላውን ለመምሰል ከሞከርን እጣችን በጊዜ መጠውለግ ነው። ስኬትህን ከሌላው ሰው ስኬት ጋር አታፎካክር፤ ደስታህን ከሌላው ሰው ደስታ ጋር አታነጻጽር፤ ይህንን የንጽጽር ክፉ ዛፍ ነቅለን መጣል እስካልቻልን ድረስ ከራሳችን ጋር ተዋህደን ንጹህ ደስታን ለማግኘት ይከብደናል።

One thought on “በኑሮ ቅርንጫፍ ላይ የተንጠለጠልን ቅጠሎች!!!

  1. Mistre,That’s really incredible!. I didn’t know you are an awesome writer. I just went over some of your essays on this website,and I really like them. Keep it up! Still expecting more from you.

Do you have any comments?