“እጆቼን ወደላይ አድርጋችሁ ቅበሩኝ”….ታላቁ እስክንድር

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

አፈታሪክ ይሁን እውነታ አላውቅም፤ ታላቁ እስክንድር እንዲህ አደረገ አሉ። ወደ ሞት አፋፍ መቃረቡን ሲያውቅ፤ ወዳጆቹን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው “ስትቀብሩኝ፤ እጄን ወደላይ አርጋችሁ ቅበሩኝ” አለ። ሰዎቹም ግራ ገብቷቸው ለምን እንደሆነ ጠየቁት፤ እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እጄን ወደላይ አድርጋችሁ ቅበሩኝ ያልኩት፤ ስሞት ምንም ነገር ይዤ እንዳልሄድኩኝ ሰዎች እንዲያዩ  ነው ” አለ

ይህንን ያለው እንግዲህ  በጊዜው አለምን ያስገበረው ታላቁ እስክንድር ነው። በክንዱ ስንቱን ያስገበረው ታላቅ፤ “ምንም ይዤ አልሄድም” ሲል ተናገረ።

“የእድሜ ሰረገላ፤ ሄዶም መቶ አይሞላ” ብሏል ዘፋኙ። አንዳንዴ የምንኖረው እስከመቼ ነው ብለን እራሳችንን ከምር ብንጠይቅ መልሱ ያስደነግጠናል። ምክንያቱም የምንጨነቀው ከምንኖረው በላይ ነው። ፈገግታን፤ ሳቅን፤ ደስታን ሳያውቁ የሚሞቱ ሰዎች ሞልተዋል። ኖረው ሳይሆን፤ ሞተው ወደ መቃብር የሚወርዱ ምስኪኖች ብዙ ናቸው። አብዛኛዏቻችን በቁማችን ሞተናል፤ ምክንያቱም መኖር ከመንቀሳቀስ እና ከመተንፈስ የጠለቀ ስሜት አለውና።

መኖር ማለት እራስን ከአሁኗ ደቂቃ ጋር አጣምሮ፤ መንፈስን፤ አይምሮን ከተፈጥሮ ጋር አዋህዶ፤ ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው የሚለውን የጠቢቡን መርህ ተከትሎ ህይወትን መምራት ማለት ነው (በጥቂቱ)። ይህ ትርጉም ለእያንዳንዳችን በልካችን መበጀት ይችላል።

አንዳንዴ እራሴን እጠይቃለው፤ የምንጨነቅለት ነገር ሁሉ ከዚህ አለም ስንሄድ ይዘነው የምንሄደው ካልሆነ፤ ምንድን ነው ነጥቡ? የብዙዏቻችን ኑሮ ይዘነው ለማንሄድ ወይም ስማችንን ከመቃብር በላይ ለማያስጠራ፤ ተራ ነገር ተሰውቷል። የቱ መቅደም እንዳለበት አናውቅም፤ እኛ ወይስ ጭንቀታችን? ቤተሰባችን ወይስ ስራችን? ሰብዓዊነት ወይስ ቁሳዊነት?  ለምርጫ የምናቀርባቸው ነገሮች እራሱ የሞኝ ሰው ድርድር ነው።

ተጨንቀን የምናጠራቅመው ገንዘብ፤ በጥላቻ የገነባነው ክብር፤ በደም ያገኘነው ስልጣን፤ በስርቆት ያካበትነው ሃብት፤ በውሸት የፈጠርነው ማንነት፤ ሁሉም ስንሞት አብረውን አይሄዱም። ያንን ማስተዋል እንዴት አቃተን? በቃ ሃቁ  ይህ ነው…….ምንም ነገር ከኛ ጋር ወደ መቃብር አብሮ አይወርድም። ይህንን ሳስብ ግርምት ያዘኝ…….እንዴት ሞኝ ነን?

ምን አልባት ስዎች ሲቀበሩ እጃቸውን ወደላይ አድርገው ቢሆን ኖሮ፤ በጥቂቱም ቢሆን ህይወታችንን እንዴት መኖር እንዳለብን ትምህርት ይሆነን ነበር። በህይውትህ የሚያስጨንቅህ ነገር ሲገጥምህ፤ እስከምን ድረስ እራስህን አሳልፈህ መስጠት እንዳለብህ ለማውቅ ሞክር፤ ምናልባት ከህይወትህ ጋር ሲነጻጸር ኢምንት ሊሆን  ይችላልና።

Do you have any comments?