“ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” አለኝ እግዜር

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

ከሁለት ሺህ አመታት በኋላ ፤ እግዜር ጥያቄውን ደገመው፤ ሊያውም ለኔ…….

የዛሬ ሁለት ሺህ አመት ገደማ፤ ፈጣሪ በምድር በነበረበት ጊዜ ሃዋሪያዎቹን ሰብስቦ ” ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል እንደጠየቃቸው አንብቤ ነበር። ሃዋርያቱም  ሰዎች አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፤ ሌሎችም  ኤሊያስ፤ ሌሎችም ኤርሚያስ ወይም ከነብያት አንዱ ነው ብለው ያስባሉ እናዳሉት ምጽሃፉ ይናገራል።

ዛሬ ከሁለት ሺህ አመታት በኋላ እግዜር ጥያቄውን ለዚህ ዘመን ሰዎች ደገመው። እንዴት እኔን መረጠኝ? እሱ እንቆቅልሽ ነው። በጽድቅ ፤ በስራዬ አልመረጠኝም፤ የመረጠኝ በዝምታዬ መሆን አለበት፤ ሲበዛ ዝምተኛ እና ታዛቢ ነኝ። እግዜር ዝምተኛ ይወዳል አሉ። ድንገት በለሊት ተገለጠልኝ፤……ከድሮ ጀምሬ እግዜርን አንድ ቀን እንደማገኘው አውቅ ነበር። ለምን እንደሆነ አላውቅም፤ በህይወቴ የምመኘው ነገር እግዜርን ማግኘት ነበር። አውቃለው ሰው ሁሉ ሲሞት ከእግዜር ጋር መገናኘቱ አይቀርም ፤ የኔ ምኞት ግን በህይወት እያለው እግዜርን ማግኘት ነበር። እናም ተሳካ!!!

ትላንት ድንግት በሌሊት እግዜር ተገለጠልኝ፤  አንድ ከባድ ጥያቄም ጠየቀኝ፤ “የዚህ ዘመን ሰዎች ማን ይሉኛል?” አለኝ። ደነገጥኩኝ በህሊናዬ ሃዋርያቱ አንድ በአንድ ትዝ አሉኝ፤ ብዋሽ ከእግዜር የሚሰወር የለም፤ እውነቱን ብናገር እግዜርን ፈራሁት ፤ ምን ልመልስ?

ዝምታዬን አይቶ እንደገና ጥያቄውን ደገመልኝ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” አለኝ። ከመመለስ ውጪ ምርጫ እንደሌለኝ አወቅኩኝ። ከማን ልጀምር? እግዜር ትክ ብሎ ሲያየኝ፤ ቶሎ መልስልኝ እና ልሂድ የሚለኝ መሰለኝ…..

“የዚህ ዘመን ሰዎች አንተን ብዙ ነገር ይሉሃል፤ ግን ማን እንደሚሉህ ሳይሆን ምን እንደሚሉህ ልንገርህ” አልኩት

“እኮ ምን?” አለኝ…..እግዜር መልሴን በጉጉት የሚጠብቅ መሰለኝ

“አንዳንዶች የለህም ይሉሃል፤” ይህንን ስል እየከፋኝ ነበር፤ እግዜርን እንዳላስቀይመው፤ ከሃጥያትም እንዳይቆጠርብኝ ፈርቼ

“ለምን የለም ይሉኛል?” አለኝ

“የለም የሚሉህ፤ እኮ ተስፋ ቆርጠው ነው፤ በዙሪያቸው ያለውን ክፉ ነገር አይተው፤ በህይወታቸው የሚገጥማቸውን መከራ ተመልክተው ፤ ዝምታህ ሲበዛባቸው የለህም ይሉሃል። ፍርድ በምድር ሲጠፋ፤ ፍትህ ከሰው ልጅ ሲርቅ፤ ፍቅር እንደ ጉም አልጨበጥ ሲል፤ ሰላም ከሰው ልጅ ሲጠፋ፤ ተፈጥሮ በሰው ሲጨክን፤ ሲጠሩህ፤ ሲጠሩህ ሳትሰማቸው ሲቀር የለህም ይላሉ”

“ሌሎች ደግሞ፤ ዳግም ሊመጣ ነው ይሉሃል፤ አለም እንዲህ ምስቅልቅሏ ሲውጣ፤ ሰው አለቅጥ መስመሩን ሲስት፤ መምጫህ ደርሶ የተዘናጋን ይመስላቸዋል፤ እናም ቀንህን ይጠባበቃሉ፤ በዙሪያቸው ያለውን ስህተት በሙሉ ካንተ መምጣት ጋር ያያይዙታል።”

“አንዳንዶች ደግሞ፤ ትቶናል ይላሉ፤ እንባቸውን የሚያብስ ሲያጡ፤ መከራቸውን የሚያሳልፍ፤ ቀንበራቸውን የሚሸከም፤ ውርደታቸውን የሚበቀል ሃይል ፤ የተጓደለባቸውን ፍትህ የሚያቃና ጉልበት ሲያጡ፤ ትቶናል ይላሉ፤ የረሳሃቸው ይመስላቸዋል፤ የሰውን ልጅ ከፈጠርክበት ጊዜ አንስቶ ሰው ከስህትቱ ባለመማሩ የተነሳ ተስፋ ቆርጠህ የዚህን ዘመን ሰዎች እንደረሳህ የሚያስቡ አሉ”

“አንዳንዶች ደግሞ ተቆጥቷል ይላሉ፤ አለም የሚሄድበትን መንገድ ሲያዩ፤ የሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን ነገር ሲያስተውሉ፤ ምድር ከተፈጥሮ የሚደርስባትን ትንኮሳ ሲመለከቱ፤ አንተ የተቆጣህ ይመስላችዋል፤ ተፈጥሮ ያንተን ቁጣ እያስተጋባች እንዳለች ያምናሉ፤ በሰው ልጅ ላይ የሚደረሰው እያንዳንዷ መከራ ያንተ ቁጣ የቀሰቀሰው እንደሆን ያስባሉ”

“አንዳንዶች ተቀይሞናል ይላሉ፤ የበደሉትን በማሰብ፤ ይቅር እንዳልካቸው የሚያውቁበት መንገድ ስለሌላቸው ብቻ፤ በጸጸት እየኖሩ ደስታ የራቃቸው አንተ ስለተቀየምካቸው ይመስላቸዋል፤ ይቅር እንዳካቸው የሚያረጋግጥ ምልክት ባለማግኘታቸው፤ በጸጸት ይኖራሉ”

“አንዳንዶች፤ በምድር ስራ ጣልቃ መግባት አትወድም ይሉሃል፤ ሁሉም ከየአቅታጫው ሲጠራህ፤ የቱንም አቤት ላለማለት ምድር እንደፍጥርጥሯ ብለህ እንደተውካት ያስባሉ፤ ጉልበተኛውን እና ደካማውን የሚገላግል ሲጠፋ፤ አንተ እንደተውካቸው ያምናሉ፤ ሰዎች በፍትህ ላይ ሲያላግጡ፤ እንተ የምድር ዳኝነትህን የተውክ ይመስላቸዋል”

ይህንን ሁሉ ስናገር ፈጠሪ ትክ ብሎ ያየኝ ነበር…..በመጨረሻ ልክ እንደ ስምዖን እኔ ምን እንደማስብ ጠየቀኝ፤ ከሱ የሚሰወር ምንም ነገር እንደሌለ ስለማውቅ እውነቱን አዝረከረግኩት

“እኔንጃ ፈጣሪ…እኔ ያለህም የሌለህም ይመስለኛል፤ ስንጠራህ ስንጠራህ ስንጠራህ አቤት ሳትል ስትቀር የለህም እንላለን፤ እኛ ሰዎች በዙሪያችን ያለው ነገር ሁሉ አልጋ ባልጋ ሲሆን ያለህ ይመስለናል፤ ግራ ሲገባን ፤ዙሪያችን ገደል ሲሆንና ጥሪያችንን አልሰማም ስትል የለህም እንላለን፤ እውነት ፈጣሪ የለህም ብንል ትቀየመን ይሆን? ጨንቆን እኮ ፤ እጅግ ፈልገንህ።

አየህ….አንተ ሳይዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው ብለሃል፤ ግን ዘመኑ ተፈታተነን፤ የምናየው ነገር፤ እምነታችንን ሚዛን እንዳይደፋ አደረገው፤ ብዙዎች ዝምታህን አይተው የለህም ብለው መንገድ ሳቱ፤ አንዳንዶች የአለምን እንዲህ መጨመላለቅ አይተው፤ እጅህን ከአለም እንዳነሳህ በማሰብ፤ ሰው መሆናቸው እረሱ፤ በተለይ ፈጣሪ መኖርህን ማን ማረጋግጥ እንደሚፈልግ ታውቃለህ?”

“ማነው ልጄ?” አለኝ፤ ምንም እንኳን የማስበውን ማወቅ ባይሳነውም

“በስቃይ ያሉት፤ በመከራ ያሉት፤በሃዘን የቆዘሙት፤ ፍርድ የተዛባባቸው፤ ጌታ ሆይ ለነሱ ስትል መኖርህን ለሁሉም አሳውቅ፤ ለተዋረዱት ስትል ጉልበትህን አሳይ፤ አንተ የለህም ብለው አንዳንዶች አለቅጥ ሃይል ያዙ…….እንደውም ፈጣሪያችሁ የት ነው? ብለው አላገጡብን፤ እስቲ አቤት ይበላችሁ ብለው በጥሪያችን ተሳለቁብን…….አዎ ጌታ ሆይ፤ ሰዎች ምን እንደሚሉህ እንድነግርህ ነበር አይደል የጠየቅከኝ…..ብዙዎች የለህም እያሉ ነው…….እባክህ አሳፍራቸው፤ እባክህ የሚያምኑብህን አሸናፊ አድርጋቸው፤ እባክህ ተስፋ የቆረጡትን ተስፋ ሁናቸው፤ ዝም አትበለን……እባክህ”

ሃሳቤን በሃይለ ቃል አጠናቀቅኩት፤ በስሜት ፈጣሪን የተዳፈርኩት መሰልኝ እና ደነገጥኩኝ፤ ከምንም በላይ አሳባቂ የሆንኩኝ መሰለኝ፤ ለነገሩ እኔ ባልናገርስ ማወቁ የት ይቀራል? ላቤ እንደጉድ ተንቆረቆረ፤ ፊቴን ቅዝቃዜ ተሰማኝ፤ ለካ ትራሴ በላብ ተጠምቆ ኖሯል፤ ሙሉ በሙሉ የቀሰቀሰኝ ግን ይህ ድምጽ ነበር፤

“አንተ እስካሁን ተጋድመሃል……”  ማዘር ከቤተክርስትያን መመለሷ ነበር….አይኔን ስገልጥ ከፊት ለፊቴ የእግዚያብሄርን ስዕል  አየሁት…..በአካል እና በስዕል ይለያያል ልበል?

Do you have any comments?