“ላለው ሁሉ ይሰጠዋል ይበዛለትማል……ከሌለው ግን ያው ያለውም እንኳን ይወሰድበታል”

Posted on Posted in መነቃቂያ

ይህንን አባባል ደጋግሜ ብሰማውም ትርጉሙ እሰከ ቅርብ ጊዜ እምብዛም አይገባኝም ነበር፤ Rhonda Byrne የተባለችው ጸሃፊ ግን አባባሉ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲኖረው አድርጋዋለች። ይህች አውስትራሊያዊት ፀሃፊ አለም የሚያውቃት “The Secret” ወይንም ሚስጥሩ በተባለው ብሩህ ህይወትን ለመምራት የሚያስችል የህይወት ፍልስፍናን በያዘው ስራዋ ነው። በ2012 ያሳተመችው “The Magic” በተሰኘው መፅሃፏ ደግሞ አንድ ቃል የህይወትን ትርጉም ምን ያህል እንደሚለውጥ ድንቅ በሆነ ሁኔታ ለማስረዳት ሞክራለች።

“ላለው ሁሉ ይሰጥዋል ይበዛለትማል……ከሌለው ግን ያው ያለውም እንኳን ይወሰድበታል”የሚለው ቃል መፅሃፍ ቅዱሳዊ ቃል ነው። እንደው በግልብ ከተመለከትነው ትርጉሙ “ ያለው ካለው ላይ እየተጨመረለት ሃብታም እየሆነ ይሄዳል….የሌለው ደግሞ ካለው ላይ እየተቀነሰበት ይበልጥ ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ ይገባል” የሚል ትርጉም ያዘለ ይመስላል። ፀሃፊዋ ግን በዚህ ሚስጥራዊ አባባል ውስጥ አንድ ቃል ይጎድላል ትላለች ይህም “ምስጋና” ነው።

እስቲ “ምስጋና” የሚለውን ቃል በዓረፍተ ነገሩ ጨምረን እንደገና እናንብበው

“ “ምስጋና” ላለው ሁሉ ይሰጠዋል ይበዛለትማል….”ምስጋና” ለሌለው ግን ያው ያለውም እንኳን ይወሰድበታል” የሚል ትርጉም ይሰጠናል። አንዲት ቃል ምን ያህል የተርጉም ለውጥ እንደምታመጣ በዚህ መመልከት እንችላለን።

በህይወታችን በዙ ልናሟላቸው የምንፈልጋቸው ነገሮች ይኖራሉ። የሰው ልጅ ሞኞት ማለቂያ የለውምና። ገንዘብ፤ ስራ፤ ፍቅር፤ ዝና፤ ስልጣን፤ በምኞት ቋጠሯችን ውስጥ ካካበትናቸው ጥቂቶቹ ናቸው። መመኘቱ ባልከፋ …..ነገር ግን ብዙዎቻችን የሌለንን ስንመለከት ያሉንን ነገሮች ዓይን እንነፍጋቸዋለን ስለዚህ መጠየቅ እንጂ ማመስገን ይሳነናል፤ ልብ በሉ ምኞቶቻችን ሁሉ ሊሳኩ የሚችሉት ባለን ነገሮች መጀመሪያ መደሰት እና ማመስገን ስንጀምር ነው። ለምሳሌ አንድ ወዳጃችን በችግራችን ደርሶ እረዳን እንብል፤ ላደረገልን እርዳታ ምስጋና ካልሰጠነው እንዴት ብሎ በሌላ ችግራችን ይደርስልናል?፤ ህይወትም ከዚህ የተለየ ባህሪ የላትም፤ ላደረገችልን ነገር ባመሰገንናት ቁጥር ያለ እርህራሄ ሌሎች ምኞታችንን ታሳካልናለች።

“በቂ ገንዘብ አላገኝም”፤ “ኑሮዬ ምስቅልቅሉ የወጣ ነው” ፤ “መልካም የትዳር አጋር አላገኘሁም”፤ “ስኬታማ አይደለሁም” የሚሉ አሉታዊ አስተሳሰቦች፤ ያለንን ነገሮች እንዳናይ የሚደነቀሩ እንቅፋቶች ብቻም ሳይሆኑ ሌሎች የማንፈልጋቸውን የህይወት አጋጣሚዎችንም መሸለም አቅም አላቸው። ብዙዎቻችን ግን ይህንን አንረዳም። ለደቂቃ ልቦናችንን ሰብስበን ካስተዋልነው እያንዳንዶቻችን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንኳን፤ ልናመሰግን የምንችልበት ብዙ ምክንያቶች አሉን። እንደው ዋጋቸውን እያራከስን ነው እንጂ እያንዳንዶቻችን ሌሎች የሚመኟቸው ነገሮች እኛ ጋር ዋጋ አጥተው ተቀምጠዋል። ለምሳሌ የአልጋ ቁራኛ የሆነ ሰው በህይወቱ የሚመኘው ነገር ሙሉ ጤንነትን ሆኖ ሳለ፤ ጤነኛው ሰው ግን ስላለው ጤና አለማመስገኑ አይገርምም?

ካስተዋልነው አንዲት ቃል ህይወታችንን በርግጥም ትለውጣለች…..ለጠቢብ አንዲት ቃል ይበቃዋል ይባል የለ

“ምስጋና ላለው ሁሉ ይሰጠዋል ይበዛለትማል….ምስጋና ለሌለው ግን ያው ያለውም እንኳን ይወሰድበታል” የሚለው ህግ ያልተፃፈ ነገር ግን አለም ሁሉ የሚመራበት ህግ ነው፤ ሁላችንም ለተሰጠን ማንኛውም መክሊት መጀመሪያ ምስጋና እናቅርብ ያኔ…ሌሎች ምኞቶቻችንን ለመጠየቅም አያስፈራንም…..ውለታውን አክብደን ያመሰገንነው ሰው እርዳታውን እንደማይሰስት ሁሉ ህይወትም ስለሰጠችን ነገር ካመሰገንናት ባለን ላይ ለመጨመር አታመነታም…..

Do you have any comments?