ህይወታችንን በራሳችን ቁጥጥር ስር ለማድረግ የሚረዱን መንገዶች-ክፍል ፪

Posted on Posted in መነቃቂያ

ለራሳችን ምን ያህል ጊዜ እንሰጣለን?

ኑሮዋችን ከጊዜው ጋር ይበልጥ እሩጫ እየሆነ መሄዱ እርግጥ ነው። አብዝተን ስራ እንሰራ ይሆናል፤ ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፋችን ግድ ነው፤ ጓደኝነትም የራሱን ጊዜ መውሰዱ አይቀርም። ግን በዚህ መሃል፤ ከሁሉም በላይ አስቀድመን ጊዜ ልንሰጠው የሚገባውን ሰው የረሳነው አይምስላችሁም? ይህ ሰው የገዛ እራሳችን ነው። ለራሳችን ምን ያህል ጊዜ እንሰጥ ይሆን?

ለራስ ጊዜ መስጠት ማለት፤ ከግርግሩ ህይወታችን ለትንሽ ደቂቃ ዞር ብለን ከራሳችን ጋር መሆን ማለት ነው፤ እራሳችንን ማማከር፤ ማየት፤ መመርመር፤ መፈተሽ። ያ ማለት ከሰው ጋር መሆን  አይጠቅምም ማለት አይደለም። ለምንድን ነው ከራሳችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያለብን ካላችሁ …..የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በሏቸው።

  • ለራሳችን ጊዜ ስንሰጥ- ፍላጎታችንን ይበልጥ ማወቅ እንችላለን። ውስጣችንን፤ ወይም ደመነፍሳችን የሚንገረንን መስማት እንችላለን። ብዙዏቻችን ኑሮዋችን የጥድፊያ ስለሆነ፤ ውስጣችንን መስማት ያቅተናል፤ ከራሳችን ጋር እየተራራቅን እንመጣለን። ከእኛ ይልቅ የሌላው ሰው አመለካከት እና ሃሳብ እኛን ይቆጣጠረናል፤ ምክንያቱም ለራሳችን ጊዜ ሰጠተን፤ የውስጣችንን ፍላጎት አላዳመጥንማ።
  • ከራሳችንን ጋር ግልጽ እንድንሆን ያደርገናል- ብዙዏች እንደሚሉት ከሆነ በራሳችንን እንዳንተማመን ከሚያደርጉን ምክንያቶች ውስጥ ዋነኛው ለራሳችን ግልጽ አለመሆን ነው። ለራሳችን ግልጽ አለመሆን ስህተቶቻችንን እንዳንቀበል እና ለውጥ እናዳናመጣ እንቅፋት ይሆናል። በህይወታችን ምንም አይነት ለውጥ ከማምጣታችን በፊት፤ ለራሳችን ግልጽ መሆን ይቀድማል። ከሰዎች ጋር ስንሆን፤ ማስመሰሉ ቀላል ነው፤ ሰዎች ውስጣችንን ማንበብ ስለማይችሉ፤ እንሱን ማታለሉ አይከብድም። ከራሳችን ጋር ስንሆን ግን እራሳችንን ማታለል በፍጹም ቀላል አይደለም። ብዙ ሰዎች ቀን በሰው መሃል ደምቀው፤ ማታ ቤታቸው ክፍላቸው ውስጥ እውነተኛ ማንነታቸው በገሃድ ሲጠብቃቸው እና ሲያስጨንቃቸው ይታያል። እንደዚህ አይነት ሰዎች፤ እራሳቸውን በሰው፤ በመጠጥ፤ በሱስ ይደብቃሉ፤ ከራሳቸው ሽሽት። ለራሳችን እረፍት መስጠት የምንፈልግ ከሆነ ለራሳችን ግልጽ መሆን አለብን። አዎ ከባድ ነው ……ግን ግድ ይላል።
  • ለራሳችን ጊዜ ስንሰጥ- ለራሳችን ይበልጥ ቅርብ እንድንሆን ያደርገናል። “You yourself, as much as anybody in the entire universe, deserve your love and affection” Gautama Buddha:: ከራሳችን የቀረበ ማን አለን? ለራሳችን ፍቅር እና እንክብካቤ በሰጠን ቁጥር፤ ሌሎችም እኛ ለራሳችን ባበጀነው ልክ መሰረት ያስተናግዱናል። እኔ ዋናው ነገር የሚመስለኝ፤ ለራሳችን ቅርብ ስንሆን እና ለራሳችን ተገቢውን እንክብካቤ ስንስጥ፤ ከሌሎች ሰዎች ተጽዕኖ ለመውጣት መንገዱ ቀለል ይልልናል። ከምንም በላይ ለምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ የሌላውን ሰው ማርጋገጫ አንፈልግም፤ ምክንያቱም ከራሳችን በላይ የምንቀርበው ማን አለና።
  • ለራሳችን ጊዜ ስንሰጥ- ለመንፈሳችን እረፍትን ለመስጠት እንድችል ያደርገናል። ብዙዏቻችን ለውጫዊው አካላችን እንጂ ለውስጠኛው መንፈሳችን ብዙ ግድ የለንም። ከሰውነታችን በላይ እረፍት እና እንክብካቤን ማግኘት ያለበት ግን መንፈሳችን ነው። አካላችን የመንፈሳችን ነጸብራቅ ነው። ሰዎች ስምንት ሰዓት ተኝተው ድካም የሚሰማቸው እንቅልፍ አልጠግብ ብለው ሳይሆን መንፈሳቸው እረፍት ስላላገኘ እና ከሃሳብ ስላላረፈ ነው ይባላል። እናም ለራሳችን ጊዜ ስንሰጥ፤ አላስፈላጊ ያልሆነውን የሃሳብ ትርምስምስ ገታ ለማድረግ ውይም መስመር ለማስያዝ ይረዳናል። ከምንም በላይ ከራሳችን ጋር የተወሰነ ጊዜ ማሳላፍ፤ እረጋ ያለ መንፈስ እንዲኖረን ያደርገናል።

Do you have any comments?