ጥበብ መውለድ ያቆመችው እሷ መካን ሆና ሳይሆን ትውልዱ መክኖ ነው!

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

በመጀመሪያ ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ፤ በማህበራዊው ገጽም ላይ ሆነ በተለያዩ ቦታዎች የሰውን ስራ እና ፈጠራ እንደራሳቸው አድርገው የሚያቀርቡ ሰዎችን በማየቴ እና በመታዘቤ ነው።

በዚህ ዘመን ስነፅሁፍን እና ሌሎች የፈጠራ ስራዎችን አስመልክቶ የሚባል ነገር አለ፤ አዲስ የጥበብ ስራ ጠፍቷል “ጥብብ መክናለች” እያሉ ሲያዝኑ ሰምታችሁ ይሆናል። እኔ ግን ጥበብ አልመከነችም እኛ ነን መካኖቹ ባይ ነኝ ። አዲስ ነገር መስማት፤ ማየት እና ማድመጥ የሚፈልጉ ሰዎች በዚህ ዘመን እምብዛም አዲስ ነገር አለመስማታቸው እና አለማየታቸው “ጥበብ መክናለች” ብለው እንዲደመድሙ ያደረጋቸው ይመስለኛል። ድሮ የተሰሩ ስራዎች እንደገና እየተቦረሹ ሲቀርቡ፤ የሌሎች ሰዎችን ስራ ሌሎች እንደኳስ እየተቀባበሉ ሲጫወቱበት እንዴት አዲስ ስራ መፍጠር ይቻላል? እንዴትስ አዲስ ጥበብን መውለድ ይቻላል?

ጥበብ መክናለች አትበሉ እኛ ነን መካኖቹ

የጥበብ ሰው ነኝ የሚል ሰው፤ ጥበብን አርግዞ፤ ምጧን ችሎ መውለድ የሚችል ብቻ ነው። የተወለደውን የጥበብ ፍሬ፤ የኔ ብሎ መጥራት አንድን ሰው ጠቢብ አያሰኘውም ባይ ነኝ። በተለይ በዚህ ጊዜ አዲስ ዛፋኝ ተብለው የሚመጡት አብዛኛዎቹ ዘፋኞች የድሮን ዘፈንን እንደ አዲስ በመዝፈን የሚታወቁ ናቸው። እርግጥ ነው የድሮን ነገር የማስታወስ ትልቅ ሃላፊነት አለብን፤ ነገር ግን ይህ ትውልድ ምን ሰራ ቢባል መልስስ አለን? ምን አሻራ ጥሎ አለፈ ቢባል የምንሰጠው ማስተባበያ ይኖረን ይሆን?

እውነተኛ የጥበብ ሰው፤ ለሌሎች ሰዎች ፈጠራ ክበር አለው፤ ምክንያቱም ምጡን እሱም አምጦት ስለሚያውቅ። በግርግር ታዋቂ ለመሆን የሚጥሩ አሳች መሲህ ፀሃፊያን ግን፤ ለጥበብም ሆነ ለፈጣሪዎቹ ክብር የሌላቸው ናቸው፤ ሃሳብን መጋርት መብት ነው፤ ምክንያቱም እኔ ያሰብኩትን ሃሳብ ሌላም ሰው ሊያስበው ይችላልና። ነገር ግን ቃላቱን፤ ዜማውን ፤ምቱን፤ ሁሉንም ያለፈቃድ መውሰድ ግን ለኔ ሌብነት ነው። አንዳንዴ ይህንን እታዘባለው፤ ፊልሞቻችን ሁሉም ሮማንስ ኮሜዲ፤ ዘፈኖቻችን ሁሉም የታደሱ የድሮ ዘፈኖች፤ ፅሁፎቻችን ሁሉ ትዝብቶች፤ ተዋንያኖቻችን ሳይቀሩ ተመሳሳይ፤ ለምን ሆኑ? ምክንያቱም የኛ ትውልድ ቀድሞ በተቀደደው ቦይ መፍሰስ ስለሚቀለው ነው። አዲስ ቦይ መቅድድ ይከብዳላ!

እኔ ማንንም ሰው የመውቀስም ሆነ የማስተማር ችሎታው የለኝም።ነገር ግን እውነተኛ የጥበብ ተቆርቋሪዎች ነን ካልን፤ ጥበብን ከመሞት የምንታደጋት፤ የራሳችንን ስራ መፍጠር ሲቻለን ብቻ ነው። ገበያው ወደ ደራበት ሳይሆን፤ ነፍሳችን ወዳመነችበት እና ወደ ተጠራችበት ቦታ እንሂድ ያኔ አዲስ የጥበብ ስራዎች ይወለዳሉ። አዲስ ግጥሞች፤ አዲስ ተውኔቶች፤ አዲስ ፊልሞች፤ አዲስ መፅሃፎች ይፈጣራሉ፤

ጥበብ መክና አታውቅም፤ ወደፊትም አትመክንም፤ አዲስ ልጆችን በኛ ዘመን መፍጠር የተሳናት፤ እኛ ጥበብን ማስወለድ ያቃተን መካኖች ስለሆንን ነው። አዲስ ነገር መፍጠር ያቃተን፤ አዲስ ቦይ መቅደድ የተሳነን መካኖች ሆነናል። ዘመን መሻገር የሚችል ስራ አዲስ ፈጠራ ብቻ ነው፤ የተፈጠረውን ነገር በማስመሰል የሚፈጠር ሌላ ማንኛውም አይነት ስራ፤ እስኪቀዘቅዝ የሚበላ፤ ሲቀዘቅዝ ገን የሚደፋ ምግብ ነው፤ ደግመው ደጋግመው የማይጎርሱለት ቶሎ የሚሰለች ፤ ምግብ። እናም ጥበብ የመከነች ከመሰለቻችሁ ተሳስታችኋል ………የመከነው ትውልዱ ነው። የመከነው ፀሃፊው፤የመከነው ሰዓሊው፤ ዘፋኙ ደራሲው ነው ጥበብን ማስወለድ ያቃተው……ጥበብማ መቼም መቼም አትመክንም። ለበዓሉ ግርማ የወለደች ጥበብ፤ ለሌሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የወለደች ጥበብ፤ ለሎሬት አፈወርቅ ተክሌ የወለደች ጥበብ፤ በኛም ትውልድ ልዩ የጥበብ ፍሬዎችን ማፍራት አይሳናትም።

ምዕራብያውያን ስለብዙ ነገሮች የተፃፉ ስራዎች፤ ስለ ተለያዩ ሀሳቦች የተዘፈኑ ዘፈኖች፤ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ተደጋጋሚ ያልሆኑ ፊልሞችን መስራት የተቻላቸው፤ አዲስ ነገር ለመፍጠር በመድፈራቸው ነው። እኛ ግን ወደ ቀለለው መንገድ ስናመራ፤ ቀድሞ ወደተቀደደው ቦይ ስንፈስ ጥበብን አመከንናት! የሰው ስራ እንደኳስ ስንቀባበል፤ ጥበብን ያለ ልጅ ያለፍሬ ዘመን እንድትሻገር ፈረድንባት!!!!

አናም እንደኔ ጥበብ አልመከነችም…..የመከንነው እኛ ነን ባይ ነኝ!!

Do you have any comments?