የፈቃድ ባርነት

Posted on Posted in መነቃቂያ

የባርነትን ታሪክ ለሚያውቀው፤ ቢደበዝዝ እንኳን የማይጠፋ ቁስል ነው። እኔ እንኳን በዚህ ፅሁፍ ለማንሳት የፈለግኩት የጥቁሮችን የባርነት ታሪክ ሳይሆን፤ እኔ እና እናንተ ያለንበትን የፈቃድ ባርነት ልብ እንድንለው ስለፈለግኩኝ ነው። የኛ ባርነት፤ ጥቁሮቹ ላይ እንደተፈፀመው ያለፈቃድ የሆነ ግፍ ሳይሆን፤ በገዛ ፈቃዳችን የተዘፈቅንበት ባርነት ነው።

ጨቋኞቻችን ቢለያዩም እንኳን፤ አብዛኛዎቻችን የፈቃድ ባሪያዎች ሆነን፤ የምንፈልገውን ሳይሆን የማንፈልገውን ኑሮ እንኖራለን። ይህ ጥሪ የሃዘን፤ የጭንቀት፤ የፍርሃት፤ የቅናት፤ የስንፍና፤ የመጥፎ አስተሳሰብ፤ የሱስ ……..የፈቃድ ባሪያዎች ለሆንን ሁሉ…..የነፃነት አዋጅ አብረን እንድናውጅ የተደረገ ጥሪ ነው። ምን አልባት ባሪያ መሆናቸውን የማያውቁ ብዙ የፈቃድ ባሪያዎች ሞልተዋል።

የፈቃድ ባሪያዎች ነን ያልኩት፤ ሁሉም ሰው የመደሰት እና የሚፈልገውን ኑሮ የመኖር መብትም ሆነ አቅም አለው ብዬ ስለማስብ ነው። ችግር ፈተና እና ውድቀት እርግጥም የሚገጥሙን ውጊያዎች ናቸው። የፈቃድ ባሪያዎች የምንሆንላቸው ከጦርነቱ በኋላ ጦር ሜዳውን ለቀን መውጣት ሲሳነን ነው።

አይምሮዋችን ያለውን ሃይል ብዙዎቻችን አናውቀውም እንጂ፤ አለምን አሁን ያለችበት ቦታ እንድትደርስ ያደረጋት ምንም ሳይሆን የሰው ልጅ አይምሮ ነው። ይህንን ማድረግ የሚቻለው አይምሮ አንተን ከማትፈልገው ግንኙነት፤ ከምጠላው ስራ፤ ከሚጨቁንህ ሱስ፤ ከሚረብሽህ ጭንቀት ማስወጣት የማያስችል ይመስልሃል? አሁን ያለንበት ማንኛውም አይነት ባርነት……በፈቃዳችን የተዘፈቅንበት ነው። የነፃነት ካቴናችንን በጉያችን ይዘን የነፃነት ያለህ እያልን ይምንዞር ምስኪን ባሪያዎች ነን………ደስተኛ ሰዎች ደስተኛ ሆነው ተፈጥረው ሳይሆን፤ ያሉበትን ሁኔታ መለወጥ እንደሚችሉ በማመናቸው ነው።

የማትፈልገውን ነገር እያሰብክ ከመብከንከን ይልቅ፤ አትኩሮትህን መፍትሄው ላይ ብታደርግ ብዙ ነገሮችን መለወጥ ይቻልሃል። ዛሬም ወደፊትም ከባድ ነገሮች ያጋጥማሉ፤ ተፋለማቸው፤ አንዳንዴ ታሸንፋለህ፤ አንዳንዴ ትሸነፋለህ፤ ውጊያው ሲያበቃ ግን፤ ሽንፈትህን እያሰብክ የፈቃድ ባሪያ ከመሆን ይልቅ፤ ለሌላ ውጊያ እራስህን ለማዘጋጀት ጊዜ ውሰድ። እመን የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ማግኘት ትችላለህ፤ በመጀመሪያ ግን ለህይወትህ ሃላፊነት ውሰድ። ጊዜህን እራስህ ላይ አጥፋ። አንብብ፤ ጆሮህን ከመጥፎ ዜናዎች አርቅ፤ እራስህን ይቻላል በሚል መፈክር ለመኖር አስልጥነው።
ይህንን ጥሪ ለመሳተፍ የምትፈልጉ ሁሉ……..ከፈቃድ ባርነት ለመውጣት ነገ ሳይሆን ዛሬ እንንቃ!

Do you have any comments?