እኔ እና “እኔ”

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

ሳልቀጥረው ነው የመጣው። ሳይቀጠር የሚመጣ እንግዳ ችር ወሬ ይዞ የሚመጣ አይመስለኝም። ለሁሉም ነገር ተዘጋጅቼ መጠበቅን ልምዴ አድርጌዋለው። እናም “እኔ” ዛሬ ሳልጠብቀው፤ ሳልቀጥረው፤ ሳይነግረኝ ብቅ አለ። “እኔ” ሳይታሰብ ፊቴ ቆመ። ምን ዜና ይዞልኝ እንደመጣ ከፊቱ ለመገመት አልቻልኩም። ፊቱ ላይ ምንም አይነት ሰሜት አይታይም፤ ደስታም ሆነ ሃዘን አይነበብም። ባዶ ስሜት….ባዶ ገፅታ….ባዶ መንፈስ። ሁሌም እንደምሸሸው ስለሚያውቅ በቀጠሮ አይመጣም፤ ድንገት ከተፍ ይላል እንጂ፤ ዛሬም እንደልማዱ እርግጠኛ ነኝ ለወቀሳ ነው የመጣው……
መንደርደሪያ ሳያስፈልገው ወደ ቁምነገሩ ገባ

“መተማመን ጠፋ?” አለኝ። የባዶ ስሜት ይነበብበት የነበረው ገፅታው…..የትዝብት መንፈስን እየተላበሰ። የበላሁት አደራ እንዳለ ሁሉ የታዘበኝ መሰለኝ……በእርግጥ ብዙ አደራዎችን በልቼበታለው
“እኔ”ን በጣም ብቀርበውም፤ ወቀሳውን አልችለውም። የሌሎች ወቀሳ ቢደማመር እንኳን “እኔ” እንዲሰማኝ የሚያደርገውን ያህል ስሜት ማናቸውም ሊያሰሙኝ አይቻላቸውም።

“ታዘብኩህ…….አንተ ከከዳኸኝ ማን ላምን እችላለው? አንተን ተማምኜ ወደላይ ከወጣሁኝ በኋላ ተመልሼ እንዳልወርድ እንዴት መሰላሉን ትነጥቀኛለህ? አንተን አምኜ የጀመርኩትን ጦርነት እንዴት ብቻዬን ታጋፍጠኛለህ? ካንተ የቀረበ ማን አለኝ” ፊቱ ይበልጥ ጭጋግ ሲለብስ ታወቀኝ
የ “እኔ” ወቀሳ አሁንስ ገደለኝ። የትዝብት አይኑ፤ የሚረጭብኝ የሃዘን ጨረር ህሊናዬን ሲያቆስለው ይታወቀኛል፤ እንባው ወኔዬን ሲሸረሽረው ይሰማኛል፤ በኔ ተስፋ ማጣቱ በፍርሃት ያርደኛል።

“አየህ……….እኔ በሰጠሁህ መሬት፤ ባዕድ እንዲጨፈርበት ፈቀድክ……አይምሮህ ላይ እንዲገነባ ያሰብነው እምነትህ ላይ፤ ሌሎች ወሻቸውን ሲቆፍሩበት ዝም አልክ። ንቀኸኝ ነው……ሁሌም ሄድኩኝ እያልኩኝ ስለምመለስ፤ ኩርፊያዬን ለመድከው። ቃልህን ባፈረስክ ቁጥር ሌላ እድል መስጠቴ…..ውሳኔ ቢስ አስመሰለኝ። ከውሳኔዎችህ እንዳትሸሽ አጥብቄ መያዜ……አጉል ወግ አጥባቂ ሆኜ የምጎተጉትህ መሰለህ….”
“እኔ” ከልቡ አዝኖብኛል፤ ከዚህ በፊት አስከፍቼው ባውቅም…..እንዲህ እንደዛሬው ተናግሮኝ አያቅም። እውነቱን ለመናገር በድዬዋለው…. “እኔ” ቢከፋብኝም ሁሌም ተመልሶ ያናግረኛል ብዬ ስለማስብ፤ ከሱ በፊት የሌሎችን ፍላጎት ለማሟላት እጥራለው። “እኔ” ካስገባኝ ቃልኪዳን በፊት የሌሎችን ቃል አከብራለው…….ምክንያቱም “እኔ” ይጨክንብኛል ብዬ ስለማላስብ። “እኔ”ን ማክበር ከተውኩኝ ቆየሁኝ…..ትህትናውን እና ለኔ ማሰቡን ስለለመድኩት። ሌሎች ፍላጎታቸውን ሳላሟላላቸው ስቀር፤ መንገዴን ይዘጉታል፤ “እኔ” ግን ሁሌም ሌላ እድል ይሰጠኛል። ሌሎች በመስፈርታቸው ለክተውኝ ካልመዘነኩ ከሰልፉ ያስወጡኛል፤ “እኔ” ግን ለኔ ምንም መለኪያ እና መመዘኛ የለውም። እናም ይህንን ስለመሳብ …..እኔ እና “እኔ” የማይቆረጥ ገመድ አለን ብዬ ስለምገምት፤ ብሎም በኔ ተስፋ ቆርጦ ጥሎኝ ይሄዳል ብዬ ስለማላስብ፤ ሌሎችን ከ”እኔ” በፊት ሳስቀድማቸው ኖርኩኝ።

“እኔ” ከሚያምንበት ውጪ ብዙ ስህተቶችን ሰራው፤ የ “እኔን” ክብር በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኝ ስል ብቻ አረከስኩት። “እኔ” ፍትሃዊ፤ ቅን፤ ቆራጥ፤ አላማ እና እምነት ያለው ሰው ካልሆንኩኝ ጥሎኝ እንደሚሄድ ቢዝትብኝም ያደርገዋል ብዬ ስላላመንኩኝ፤ ሌሎችን ለማስደሰት ስል ተልፈሰፈስኩኝ።

ዛሬ ግን “እኔ” ላይ የማየው ስሜት እውነት ይመስላል። በኔ ላይ የነበረው ተስፋ የተሟጠጠ፤ ያለቀ እንደሆነ አይኑ ያሳብቃል። ፈራሁኝ፤ ለማስረዳት እና እድል እንዲሰጠኝ ለመማፀን ስጀመር…..አፌን በመዳፉ ሸፈነው። አበቃ!!!! “እኔ” በኔ ተስፋ ቆርጦ…..ለዘመናት እንደቤቱ ከሚቆጥረው ህሊናዬ ውስጥ ጓዙን ጠቅልሎ ወጣ።

ባዶው ህሊናዬ ሊበላኝ ደረሰ…..ከ “እኔ” በፊት ያስቀደምኳቸው ሰዎች ያፅናኑኛል ብዬ ብጠብቅም፤ ይኸው ቀናቶች ተቆጠሩ፤ ማናቸውም ብቅ ሳይሉ። ለካ እነሱም እኔን ያለ “እኔ” ብቻዬን አይፈልጉኝም። እኔ ያለ “እኔ” ባዶ ነኝ። ለ “እኔ” የነፈግኩትን እውነት፤ ለሌላው ብሰጠውም ምንም ዋጋ የለውም፤ ከ “እኔ” ሸሽጌ ለሌሎች የምቸረችረው እምነት ለካ ከንቱ ነው። ባዶነት ገነጣጥሎ ሊበላኝ ነው…..ከ”እኔ” የምር ስርቅ ሁሉም…..ከኔ መራቅ ጀመረ።

ህሊናዬን ሸሽቼ ጎዳና ላይ ወጣሁኝ ፤ “እኔ”ን ፍለጋ….ምን አልባት አንድ ለክፉ ቀን ደብቆ ያስቀመጣት እድል ትኖረው ይሆናል፤ ፈፅሞ የማላበላሻት እድል። “እኔ” መልሼ እስካላገኘሁኝ ድረስ……ለኔ መኖር ከንቱ ነው…..ይቅናህ በሉኝ።

Do you have any comments?