ከቶ ይህች ውበት ምን ትሆን?

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

ውበትን ሲያደንቋት ሲያሞግሷት፤ ሲስሏት ሲክቧት፤ ስሰማ ላያት ጓጓሁኝ። እሷን ፍለጋ ስዳክር ከርምኩኝ……ወደ ውበት እንዲመሩኝ የጠየቅኳቸው ሰዎች ወደ መሩኝ ስፍራ ሄጄ እነሆ ይህንን ታዘብኩኝ።

በመጠጥ ለናወዘው፤ የምሽት ህይወት ልቦናውን ለሰወረው ውበት ከሴት ገላ ላይ የምትቀጠፍ በለስ ናት። ውበት እንደ ሸንበቆ አካል እንጂ ውስጠት የላትም፤ ባዶ ናት። እሱም ከአካሏ ውጪ አያሰኘውም። ውበት ለሱ ከመጠጡ ከዘፈኑ፤ ከወሲቡ፤ ከኳኳታው መሃል የምትጣል የማትፈለፈል እንቁላል ናት። ዘወትር በምሽት የሚታቀፋት፤ ቀን ቀኑን የሚረሳት፤ ነፍስ የሌላት እንቁላል።

ተፈጥሮ ላንበረከከችው ደግሞ ውበት የማትበላ ወፍ ናት። መምጫዋ የማይታወቅ ብቅ እያለች ስሜትን የምትገዛ። አንዳንዴ ከሰማዩ ከደማናው መሃል ብቅ ትላለች፤ አንዳንዴ ከፀሃይ ጋር ፍንጥቅ ትላለች፤ ሲያሰኛት ከጨረቃ ጋር ተኮራምታ ያገኛታል፤ አንዳንዴ ከጫከው ውስጥ ከአውሬው ጋር ተስማምታ ታስደነግጠዋለች። በባህር ስትቀዝፍ ሲያያት ቆይቶ በየብሱ ስትዳክር ያገኛታል። ሲያሻት በዝምታ ትታጀብና ትመጣለች፤ መልሳ ደግሞ በጩኸቱ ሸኙኝ ትላለች። ግራ ስታጋባው ለብቻው ትገለፅለታለቸ፤ ሲመቻት ደግሞ በሰው መሃል እንግዳ ሆና ትጠብቀዋለች። ለእሱ ውበት መንፈስ ናት ባሻት መልክ የምትመጣ። ግራ ብታጋባውም ባህሪዋን በፀጋ ይቀበላል፤ ምርኮኛ ነዋ።

ህይወት ለምታጣድፈው ደግሞ ውበት ግብ ናት። እሮጠው የሚደርሱባት፤ አቀበት ወጥተው፤ ቁልቁል ወርደው የሚያገኟት። በድል እሳት የምትፈጠር ፍም።ካልደከመ የማትጨበጥለት ይመስለዋል። ቅርብ ብትሆንም፤ እሩቅ እየመሰለችው መንፈሱን ያደክማል። ከበራፉ ቢያገኛት እንኳን……ልብ ብሎ አያያትም፤ ጥሏት ሄዶ ስሟን ይጣራል፤ ቅርብ ሆና እሩቅ እየመሰለችው። ውበትን ሊያገኛት ቢወድም ሁሌም በመንገድ ይተላለፋሉ፤ አይተያዩም።

ለጠያቂው ውበት መልስ ናት። ለምንም ጥያቄ የምትሰጥ መልስ። ሲመራመር ውበትን እየፈለገ ነው፤ አንዱ ጥያቄ ሌላ ጥያቄ እየፈጠረበት፤ ውበት እንደጥላ ትከተለዋለች እንጂ አይጨብጣትም። ያያታል እንጂ አይዳስሳትም፤ እንደሃረግ የሚረዝመው ጥያቄው ወደ ውበት የሚያደረሰው መንገዱ ቢመስለውም እውነታው ግን ሌላ ነው። በጥያቄ የተቦረቦረው መንገዱ ወደ ውበት የሚያደርሰው ሳይሆን የሚያርቀው ነው። ቢሆንም ተስፋ አይቆርጥም፤ ይጠይቃል…..ውበትን ፍለጋ ይዳክራል።
ለአማኙ ውበት እምነቱ ናት። በመዳፉ ይዞ የማይለቃት ታላቅ ቅርሱ። በምን እንዳገኛት ባያውቅም፤ መዳፉ ላይ እስካለች ድረስ ሊለቃት አይሻም። ውበቱ ደስታው ናትና። በሄደበት አብራው የምትሄድ፤ ከእሷ ሌላ መኖሯን የማያውቅ፤ ለእሱ ብቻ የምትገለፅ ሚስጢሩ።

በመጨረሻ እራሴን እንዲህ ስል ጠየቅኩኝ።ይህች ውበት ከቶ ምንድን ነች፤ ሰው እንደ አስተሳሰቡ የሚፈጥራት የነፍሱ ስባሪ ትሆን እንዴ?

Do you have any comments?