“ሰባቱ እኔነቶቼ”……ካህሊል ጂብራን

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

“the mad man” ከተሰኘው መጽሰሃፉ ላይ “the seven selves” የተሰኘው ጽሁፍ እንዲህ ተተርጉሞ ቀርቧል

እንደ ሞት ያለ ጸጥታ ባለው ጨለማ ውስጥ በግማሽ ልቤ ተኝቻለው። ጨለማ ከጸጥታ ጋር ሲደመር እጅጉን የሚያስፈራራ ይመስላል። እንቅልፍ ቢወስደኝም እንቅልፌ የከበደ አልነበረምና፤ ከጎኔ ተቀምጠው ሰባቱ ማንነቶቼ ሲንሾካሾኩ ይሰማኛል።
አንደኛው ማንነቴ እንዲህ ሲል ሰማሁት “ እዚህ እብድ ሰው ጋር እንደ መዥገር ተጣብቄ ለዘመናት አብሬው ኖርኩኝ፤ ህመሙን እንዲድን ሳይሆን እንዲያገረሽበት ሳደርግ፤ ስቃዩን በቀን ሃዘኑን በማታ እያደስኩበት አብሬው ከረምኩኝ፤ እነሆ ቢበቃኝ ይሻላል፤ ከዚህ በኋላ አብሬው ልኖር አይቻለኝም” ይህንን ተናግሮ ሲጨርስ ፤ ሁለተኛው ማንነቴ ቱግ ብሎ እንዲህ ተናገረ

“ ምነው ወዳጄ? ከኔ ህይወት ያንተ በእጅጉ ይሻላል፤ ወንድሜ እኔ ከዚህ እብድ ሰው ጋር ሲስቅ አብሬ ስስቅ፣ በደስታው ሁሉ አብሬው ስደሰት ፣ ከደስተኛ ህይወቱ ሌላ ምኑንም ሳልካፈል ይኸው እድሜውን በሙሉ አብሬው ኖሬአለው፣ ስለዚህ የኔ ህይወት ነውና አሰልቺ እኔ ባምጽ ይሻላል” አለ። ሶስተኛው ማንነት ሁላቸውም እንዲሰሙት በሚመስል ድምጽ ጮክ ብሎ መናገር ጀመረ

“ተው ተው እኔ ምን ልበል? እኔ የምኞቱ ደራሲ የፍላጎቱ ምንጭ ምን ልበል? ወሰን የሌለው ምኞት ሳስመኘው የማይፈታ ህልም ሳሳልመው የከረምኩት እኔ ከንቱ ማንነቱ ነኝ ከዚህ እብድ ሰው ውስጥ ማመጽ እና መውጣት ያለብኝ” ይህንን ተናግሮ ሲጨርስ ከሁሉም በላይ በሚያስፈራ ድምጽ አራተኛው ማንነቴ ንግግሩን ጀመረ፤ የድምጹ ከፍታ የኔን መተኛት እንደረሱት ይናገራል

“አትሳሳቱ ወንድሞቼ ከሁላቹህም በለይ በዚህ እብድ ሰው ላይ ማመጽ ያለብኝ እኔ ነኝ፤ እኔ ከጨላማ ዋሻ የተገኘው ክፉ ማንነቱ ነኝ፤ ልቡን በክፋት እና በጥላቻ የምሞላው ከዚህ በኋላ ግን ይህንን እብድ ሰው ማገልገል እንደሌለብኝ ይሰማኛል” አለ ከድምጹ በብሶት እንደሚናገር ያስታውቃል

“በጭራሽ” አለ አምስተኛው ማንነቴ “ እኔ ማሰብ የምችለው ማንነቱ ነኝ ከዚህ እብድ ሰው መራቅ ያለብኝ፤ እረፍት የማሳጣው፤ ብክን ያለ ኑሮ የማስኖረው የሌለውን የማሳስበው ባልተፈጠረው እንዲደመም የማደርገው እኔ ነኝ፤ ታድያ ማነው ይህን እብድ ሰው ማገልገል ማቆም ያለበት? እኔ ወይስ እናንተ?” ይህን ጊዜ ስድስተኛው ማንነቴ በንዴት መናገር ጀመረ

“እኔ የስራ ማንነቱ ብቸኛ ነኝ፤ ጉልበቴን ሳልስት ቀኑን ቀን እንዲመስልለት በስራ በታታሪነት ሳገልግለው ከርሜአለው አይኖቹ እረቀው እንዲመለከቱ፤ ምስል አልባው ማንነት ምስል እንዲይዝለት ስለፋ የከረምኩት እኔ ብቸኛው ነኝ ከዚህ እብድ ሰው እርቄ መሄድ ያለብኝ” አለ

ሁሉም የልባቸውን ተናገሩ፤ ለዘመናት ችለውት የነበረውን አንዳቸው ላንዳቸው ተነፈሱ፤ ማንም ዳኛ በሌለበት ብሶታቸውን አራገፉ፤ የመጨረሻው እና እስካሁን በዝምታ ሌሎቹን ሲሰማ የነበረው ሰባተኛው ማንነቴ ሊናገረው የሚፈልገው ነገር እንዳለው ለማሳወቅ ጉሮሮውን ጠረረገ

“ይገርማል እኔ እያለው እናንተ እዚህ ሰው ላይ ማመጻቹህ፤ እናንተስ የየራሳቹህ የስራ ድርሻ አላቹህ፤ ልታደርጉት የሚጋባቹህን ሁሉ ታውቃላቹህ፤ ቢያንስ የየራሳቹህ እጣ ፋንታ አላቹህ፤ እኔ ምንም የሆንኩት ማንነቱ ነኝ ማመጽ ያለብኝ፤ ወዴት እንደምሄድ አላውቅም ፤ ምን እንደምፈልግ አላውቅም፤ የስራ ድርሻዬን አላማዬን ፍጹም አላውቅም፤ እናም ወንድሞቼ እናንተስ ስራ አላቹህ በህይወቱ የራሳቹህን አሻራ ልታኖሩ ነው፤ ስለዚህ ይህን እብድ ሰው ትቶ መሄድ የምትሉትን ሃሳብ ወዲያ ጣሉት በህይወቱ ድርሻ አላቹህና” አለ ሃዘን እየገባው

ሰባተኛው ማንነቴ የሁሉንም ልብ ነካ፤ ስድስቱም በሃዘን በግማሽ ልቤ የተኛሁትን እኔን ተመለከቱኝ፤ ሰዓቱ ገፍቶ ሌሊቱ ተጋምሶ ነበረና ሁላቸውም ደከማቸው፤ እንደ ድሮ ሳይሆን በአዲስ መንፈስ ቀስ በቀስ እንቅልፍ ፈነጋላቸው፤ ከሰባተኛው ማንነቴ በቀር ፤ እሱ ሁሉንም በትካዜ ይመለከት ነበር

ሰው አንድ አካል ሆኖ ይፈጠር እንጂ ውስጡ ብዙ ማንነቶች እንዳሉት እኔም እንደ ካህሊል ጅብራን አምናለው። ደግ ማንነት አለን፤ እራስ ወዳድ ማንነት አለን፤ ታታሪ ማንነት አለን፤ ሰነፍ ማንነት አለን፤ ታማኝ ፤ከሃዲ፤ አሩቅ አሳቢ፤ ቅርብ አላሚ፤ በተስፋ የሚኖር፤ ተስፋ የቆረጠ ከዚህም በላይ ብዙ መልክ ያላቸው ብዙ ማንነቶች አሉን፤ ዋናው ቁም ነገር ግን የትኛው ማንነታችን ነው መሪ ነው? የሚለው ነው።

One thought on ““ሰባቱ እኔነቶቼ”……ካህሊል ጂብራን

Do you have any comments?