ምን አልባት በልጅነት ገመዳችን ይሆን እስካሁን የታሰርነው?

Posted on Posted in መነቃቂያ

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ዝሆኖች ታስረው በሚገኙበት ስፍራ እያለፈ ሳላ አንድ ነገር ቀልቡን ይስበውና ይቆማል። እነዛ ግዙፍ የሆኑ እንስሳት ያለ ብረት፤ ያለ ሰንሰለት የፊት እግራቸው ላይ ብቻ በታሰረች ትንሽ ገመድ ተይዘው ሲያይ ግራ ገባው። በማንኛውም ሰዓት ማምለጥ ይችላሉ፤ ነገር ግን አያመልጡም። ግርምቱን ዝሆኖቹን ይንከባከብ ለነበረው የዝሆኖቹ ጠባቂ አጫወተው።

ጠባቂውም እንዲህ ሲል አስረዳው “ አሁን ታሰረውበት የምታየው ገመድ፤ ህፃን ሆነው በትንሽነታቸው ታስረውበት ከነበረው ገመድ ጋር አንድ ነው፤ ትንሽ እያሉ ገመዱ በእርግጥም አጥብቆ ይይዛቸው ነበር። እያደጉ ሲመጡም ያንን ገመድ በጥሰው ማምለጥ እንደማይችሉ አይምሮዋቸው ያምናል፤ ስለዚህ ምንም ትልቅ ቢሆኑና ማምለጥ ቢችሉም፤ በጭራሸ ለማምለጥ አይሞክሩም፤ ምክንያቱም ማምለጥ አንደማይችሉ ተደርገው ስላደጉ፤ በትንሽነታቸው አጥብቆ ይዟቸው የነበረው ገመድ አሁንም አጥብቆ እንደሚይዛቸው ያምናሉ” ብሎ መለሰለት።

ሰውየው ዝሆኖቹን በሃዘን ተመለከታቸው፤ በፈለጉት ሰዓት አምልጠው ነፃ መሆን ሲችሉ፤ አቅም እንደሌላቸው ስላመኑ ብቻ እስረኛ ሆነው ይኖራሉ።

ይህ ታሪክ ትልቅ መልዕከት አለው፤ ለዚህም ነው ተርጉሜ ላቀርበው የወደድኩት። (የታሪኩ ፀሃፊ ማን እንደሆነ አላውቅም)
ስንቶቻችን ይሆን በልጅነት ገመዳችን እስካሁን የታሰርነው? አቅም በሌለን ጊዜ የጣለን ገመድ አሁንም ድረስ የሚጥለን እየመሰለን በእስር ያለን ? ቤተሰብ እና ማህበረሰብ አጥልቆልን የነበረው ያ ቀጭን ገመድ፤ አሁንም ድረስ የማይበጠስ የሚመስለን? የገመዱ ጥንካሬ ሳይሆን የአይምሮዋችን እምነት አቅማችን እንዳንጠቀም አድርጎናል።

አንድ ሰው፤ ምንም እንኳን ብዙ ሰዎች አትችልም ቢሉት፤ ምንም ያህል ውድቀት ቢገጥመው፤ ምንም ያህል ደረጃውን ለመውጣት ቢከብደው፤ምንም እንኳን አቅሙን ሌሎች ማየት ቢሳናቸው፤ፈፅሞ እንዳይችል ሊያደርጉት አይችሉም። የሌሎች ሰዎች አቅም ልክ እኒያ ትላልቅ ዝሆኖችን አስራ እንዳስቀመጠችው ገመድ ቀጭን ነው፤ ከታገልነው እኛን አስሮ ሊያስቀረን አቅም የለውም። ከገመዱ ይልቅ ዝሆኖቹን ያሰራቸው የገዛ አይምሮዋቸው ነው፤ የገዛ እምነታቸው። እኛ እራሳችንን እስካልጣልን ድረስ ሌሎች ሰዎች በፍፁም ያንገዳግዱናል እንጂ እንድንወድቅ አያደርጉንም።

ሁላችንም እራሳችንን ለደቂቃ ብንቃኝ፤ ካለንበት የእስር ህይወት እንዳናመልጥ የያዘን በአንድ እጃችን ልንበጥሰው የምንችል ቀጭን ገመድ ነው። ከያዘን ፈርሃት፤ ከተጠናወተን የአልችልም ባይነት መንፈስ ተላቀን የታሰርንበትን ገመድ ብንመለከት፤ ምንአልባት በራሳችን እንሳለቅ ይሆናል። ውድቀታችን፤ ስኬታችን፤ ነጻነታችን፤ ባርነታቸን፤ በማንም ሳይሆን በራሳችን ውሳኔ የሚፀድቅ ነው። የምንኖርበት ኑሮ ላይ ምንም እንኳን ብዙዎች ተፅዕኖዋቸው ቢያርፍበትም፤ የመጨረሻው ውሳኔ ግን የራሳችን ብቻ ነው፤ የራሳችን ብቻ።

ሌሎች አቅማችንን እንዲወስኑት ካደረግን፤ ሌሎች ስለራሳችን እንዲነግሩን ከፈቀድን፤ በቀጭን ገመድ ታስረን ህይወታችንን መግፋታችን ነው። እውነቱን እንነጋገር….ምንድን ነው የሚይዘን ያለው? እንዳንለወጥ ያሰረን ምንድን ነው? መበጠስ እና ማምለጥ አቅቶን ነው ወይስ እንደዝሆኖቹ አንችልም ብለን ስላመንን?

Do you have any comments?