ደስተኛ ሰው ማን ነው?

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

መጠየቅ የማይሰለቸው አይመሮዬ ሁሌም መልሶ መላልሶ ከሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንደኛው ……. “ደስተኛ መሆን ምን ማለት ?” የሚለው ዋነኛው ነው።

አንድ ማን እንደተናገረው የማላስታውሰው አባባል ትዝ አለኝና ይኸው አሰፈርኩት “በልጅነቴ ፈተና ስፈተን ምን መሆን ትፈልጋለህ ተብዬ ስጠየቅ “ደስተኛ መሆን” የሚል መልስ ሰጠው…..ፈተናውን የሚያርመው አስተማሪ “ጥያቄው አልገባህም” ብሎ ተቆጣኝ…..እኔ የማውቀው ግን አስተማሪው ስለ ህይወት እንዳልገባው ነው” ይላል።
ደስተኛ መሆን የማይመኝ ሰው ይኖራል? በፍፁም! ታዲያ ለምን አብዛኛዎቻችን ደስተኛ መሆን ያቅተናል? ለምንስ ደስተኛ አለመሆናችንን ከማመን ይልቅ ከራሳችን ለመሸሽ እንሞክራለን።

በድብልቅልቁ ውስጥ እየተሹለከለክን፤ ህሊናችን እንዳይጠይቀን አይምሮዋችንን በምኑም በምኑም ጠምደን እስከመቼ እንዘልቃለን? ደስተኛ መሆን ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር ይሉት አይነት ነገር ለምን ሆነብን? መፅሃፍቱ፤ ሃይማኖቱ፤ ሳይንሱ፤ ፍልስፍናው ሁሉ ደስተኛ የመሆንን ቀመር እጅግ አቅልለው እያሳዩን ስለምን በተግባር ስንሞክረው ከበደን?

ታላቁ ፈላፍሳ ሶቅራጠስ ብዙዎቻችን ደስተኛ ለመሆን የከበደንን ምክንያት አስቀምጦልን አልፏል። ሶቅራጠስ የደስተኛነን ሚስጥር እንዲህ ይገልፀዋል “ደስተኛ ለመሆን ቁልፉ ………አትኩሮታቸንን ከስጋችን ላይ አንስተን ወደ ነፍሳችን ማድረጉ ነው” ይላል።

ደስታን ከአይምሮ ውጪ የሚፈልጋት ሰው በፍፁም ሊያገኛት አይችልም። ለዚህ ደግሞ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ሃብት ሳየኖራቸው፤ ጤንነት እየጎደላቸው ደስተኛ የሆኑ ሰዎች አይታቹህ አታውቁም? ውጫዊ ገጽታቸው ሳያምር፤ አለማዊ ፍላጎታቸው ሳይሟላ ደስተኛ የሆኑ ሰዎች አይታቹህ አታውቁም? ቤታቸው ባዶ ሆኖ፤ ዘመድ ጓደኛ እንደልብ ሳይኖራቸው ደስተኛ የሆኑ ሰዎች አይታቹህ አታውቁም?

ይህን ስናይ ደስታ በፍፁም ከቁሳዊ እና አከላዊ ነገሮች ጋር ግንኙነት እንደሌላት እናያለን። የሰው ልጅ ሁሉ ነገር ቢኖረው አይምሮው ግን ደስታን ከተራበ ምን ዋጋ አለው? ለምን ተፈጥሮ ያደለችንን የደስተኛነት ፀጋ በገዛ ፈቃዳችን ሳንጠቀምበት ህይወታችን ያልፋል? ለማመን ትንሽ ቢከብድም እንኳን እውነቱ ግን ይህ ነው……..በማንኛውም አይነት የህይወት አጋጣሚ ውስጥ ብንሆንም እንኳን ደስተኛ መሆን እንችላለን። እንዴት?

እስቲ አስቡት የጎደለን ነገር ቢኖር እንኳን ያለን እንደሚበዛ ካሰብን፤ ለሌሎች ሰዎች መልካም ነገር ማድረግን ከለመድን፤ ተስፋ ከልባችን ካልጠፋ፤ ትላንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ መለየት ከቻልን፤ በጠዋት ከምትፈካው ጀንበር ጋር አብረን ከሳቅን፤ ማታ ከምትወጣው ጨረቃ ጋር አብረን ከደመቅን፤ ከተፈጥሮ ምት ጋር አብረን ከዘፈንን፤ ከሁሉም በላይ ደስታን ከሰው ምንጭ ሳይሆን ከራሳችን የህይወት ምንጭ ለመቅዳት ከሞከርን …….እንዴት ደስተኛ አንሆንም?